የመዲናዋ ጥበባዊ መሰናዶዎች 

You are currently viewing የመዲናዋ ጥበባዊ መሰናዶዎች 

በአብርሃም ገብሬ

በመዲናዋ አዲስ አበባ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ባለፉት ቀናት ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት ከተሰናዱ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል ኪነ ጥበባዊ የፓናል ውይይቶች፣ የአዳዲስ መጽሐፍት ህትመት፣  የሥዕል ዐውደ ርዕይ፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡ 

መጽሐፍት

“የዕውቀት ዘርፉ መጽሐፍት እንዴት ይነበቡ?” በሚል ርዕስ ውይይት ሊደረግ ነው፡፡ ዛሬ ቅዳሜ ከሰዓት በአነባበብ ጥበብ ላይ የተዘጋጀ ልዩ የፓናል ውይይት ይደረጋል፡፡ በሙያቸው የታወቁ የሥነ ጽሑፍ፣ የፍልስፍና፣ የፖለቲካ ሳይንስ እና የታሪክ ተመራማሪዎች የመጽሐፍት ንባብ በየሙያው ዘርፍ እንዴት እንደሚለዋወጥ እና መጽሐፍት ሁሉ በአንድ መንገድ ብቻ እንደማይነበቡ ተንትነው ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ በውይይቱ መጽሐፍት ከአካዳሚያዊ ተግባራቸው ውጭ ስለሚያስገኙት ደስታ እና ስላላቸውም ዋጋ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

በፓናል ውይይቱ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት ኃይሉ ሀብቱ (ተባባሪ ፕርፌሰር) እና ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ከሥነ ጽሑፍ አንጻር፤ የፈጠራ ሥራን ምናብን ለማስፋት ስለማንበብ፣ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) እና አሞን በቀለ (ዶ/ር) ከፍልስፍና አንጻር ንባብ እንደ ፍልስፍናዊ ኀሠሳ እንዲሁም መሐመድ እድሪስ (ዶ/ር) አውድን እና የትርክትን ኃይል መረዳት በሚል ርዕስ ሃሳቦቻቸውን ለታዳሚያን ያጋራሉ፡፡ የፓናል ውይይቱ የሚደረግበት ቦታ 4 ኪሎ ኢክላስ ህንፃ ዋልያ መጽሐፍት አዳራሽ ውስጥ ሲሆን፣ ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓም ከሰዓት 8:00 ጀምሮ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በአንጋፋው ደራሲ ቤልጅግ አሊ(ጌዲዮን ተስፋዬ) የተፃፈው የአጫጭር ተረኮች መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው፡፡ “በእኔ ስም አይሆንም” በሚል ርዕስ የተጻፈው የአጫጭር ተረኮች መጽሐፍ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰባዊ መስተጋብር፣ እሴትና ታሪክ በኪናዊ አጻጻፍ የቀረቡበት ነው ተብሏል፡፡ ደራሲ ቤልጅግ አሊ ከዚህ ቀደም ‘ቀለበቴን ስጧት’ እና ‘ዕንባና ኩነኔ’ በሚሉ ርዕሶች ባሳተማቸው መፅሐፎቹ ይታወቃል። በዚህ መጽሐፉ ከሰፊ የህይወትና የንባብ ባህሩ የጨለፋቸው አጫጭር ታሪኮች በውብ አፃፃፍ ተሰድረው ቀርበዋል።

ሥዕል

የአእምሮ ጤና ላይ ያተኮረ የሥዕል ዐውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው። የአእምሮ ጤና ላይ ትኩረት ያደረጉ የሥዕል ስራዎች የቀረቡበት “Art inspired by mental health” የሥዕል ዐውደ ርዕይ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ስድስት ኪሎ በሚገኘው በገብረክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ሙዚየም ውስጥ ተከፍቷል።

 በስዕል ዐውደ ርዕዩ ላይ የአዕምሮ ጤና ትልቅ ትኩረት እንደሚሻ የሚያስገነዝቡ ሥራዎች የቀረበበት ነው ተብሏል፡፡ በዚህ ዐውደ ርዕይ የሠዓሊ ሰሎሜ ጌታቸውና የሠዓሊ አለማየሁ ደረሰ ሥዕሎች መቅረባቸው ኢቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል። ዐውደ ርዕዩ እስከ ፊታችን ጥቅምት 8 ቀን ድረስ ይቆያል ተብሏል።

“የተመለሱ እይታዎች” ዐውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ የሠዓሊ ኪሩቤል ተፈሪ የሥዕል ስራዎች የቀረቡበት “የተመለሱ እይታዎች” የተሰኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ ባሳለፍነው ወር መስከረም 7 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሐያት ሪጀንሲ ሆቴል ውስጥ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ እየታየ ይገኛል። የሰዓሊው የተለያዩ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች የቀረበበት የሥዕል ዐወደ ርዕይ እስከ ፊታችን ሰኞ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል ተብሏል።

ቴአትር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሑድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ፡፡ 12ቱ እንግዶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:30 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል። 11፡30 ሰዓት ደግሞ ባሎችና ሚስቶች  የተሰኘው ቴአትር በዚያው ቴአትር  ቤት ይታያል። እሑድ በ8፡30 ሰዓት ንጉሥ አርማህ፣ 11፡30 ሰዓት ደግሞ እምዩ ብረቷ ቴአትር በዚሁ በብሔራዊ ቴአትር ይታያል፡፡

በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ደግሞ እሁድ በ8:00 ሰዓት የደመና ዳንኪረኞች የተሰኘው ቴአትር ይታያል። በተጨማሪም በቀጣይ ቀናት በብሔራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review