በአብርሃም ገብሬ
ከተሜነትና ዘመናዊነት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው። ከተሜነት ሲጎለብት ዘመናዊነትም ይጎለብታል፤ የዘመናዊነት መጎልበት ደግሞ በግልባጩ የከተሜነት ዕድገት ያመጣል፡፡ በሌላ አገላለጽ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ፣ ለሰዎች ህይወት ምቹ የሆኑ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መስፋፋት፣ አማራጭ የመዝናኛ ስፍራዎች መጨመር፣ ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች የሚዘጋጅባቸው መድረኮችና የጥበባዊ ሥራዎች ማደግ የዘመናዊ ከተማ አበይት መገለጫዎች ናቸው፡፡
የዘመናዊት ኢትዮጵያ መዲና በመሆን ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ዕድሜ ያስቆጠረችው አዲስ አበባ የዕድሜዋን ያህል አልዘመነችም በሚል በተለያዩ ጊዜያት ትችት ሲቀርብባት ነበር፡፡ በተለይ የኪነ ጥበባዊ ሥራዎች የሚታዩባቸው የቴአትር ቤቶች እጥረትና የከተማው ውበት ሁኔታ ጥያቄ ሲነሳበት ቆይቷል፡፡ ለዓመታት የቆዩ ጥቂት ቴአትር ቤቶች ቢኖሩም፣ በእድሳት እጥረት፣ ዘመኑን የሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ውስንነትና ሌሎች ተጨማሪ ሲኒማ ቤቶች ባለመገንባታቸው በዕይታዊ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ዕድገት ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተሰሩ ያሉ ቴአትር ቤቶችና ተያያዥ የጥበብ ማሳያ ሥፍራ ግንባታዎች ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶችን የሚደፍኑ እንደሆኑም ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍም በከተማዋ በዘመናዊ መልክ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የቴአትር ቤቶች ለኪነ ጥበባዊ እድገትና ለወል ዕሴቶች መጎልበት ያለቸው ፋይዳ ምን እንደሚመስል በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡
ዕሴት ጭምረው የተገነቡት የመዲናዋ አዳዲስ ሲኒማ ቤቶች
“Why Cultural Institutions Need to Invest in Innovative Design” በሚል ርዕስ ‘ስቲች ዲዛይን ሾፕ’ የተሰኘ ገጸ-ድር በመስከረም 2024 ባስነበበው ሰፊ ጽሑፍ፣ እንደ ቴአትርና ሲኒማ ቤት ላሉ ተቋማት ትኩረት መስጠት ታሪኩን፣ እሴቶቹን እና ፈጠራን የሚወድድ ትውልድ እንዲፈጠር መንገድ ይጠርጋል፡፡ ዘመኑን የሚመጥኑ የጥበብ ተቋማቱ ደግሞ የማህበረሰቡን ታሪክ በመንገርና የወል ዕሴቶቹን ክሱት በማድረግ ኹነኛ ሚና ይጫወታሉ። የኪነ ጥበብ ተቋማት በየጊዜው ፈተና እንደሚያጋጥማቸው የሚያትተው ይኸው ጽሑፍ፣ አንዱና ዋነኛው ፈተናቸው ትልልቅ የህዝብ እንቅስቃሴዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ሥፍራዎች ውስንነት ነው። እንዲሁም አዳዲስ የጥበብ ትርኢቶች፣ የቴአትር ማሳያዎች፣ ትምህርታዊ ፕሮግራሞች፣ ሕዝባዊ ዝግጅቶች፣ ዘመናዊ ቴክሎጂ የተገጠመላቸው የጥበብ አዳራሾች በየጊዜው መሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ለውጥ መነሻ ያደረጉ የቴአትርና ሲኒማ ስፍራዎች መገንባት እጅግ ወሳኝ መሆኑን መረጃው ጠቅሷል፡፡ አሁን ላይ የመዲናዋ ነባር ቴአትር ቤቶችን በዘመናዊ መንገድ ከማደስ ጎን ለጎን አዳዲስ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ሥፍራዎች መገንባታቸው ይህንን ክፍተት እንደሚደፍን የጥበብ ሰዎች ትልቅ ተስፋ አሳድረዋል፡፡
ከሳምንት በፊት የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ የተገነባውን ዘመናዊ የህጻናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስን መርቀው መከፍታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ ምርቃት ወቅት ከንቲባዋ ሲናገሩ፣ የኪነ ጥበብ ታሪክ ሲወሳ አዲስ አበባ የአንበሳውን ድርሻ የምትወስድ ብትሆንም፣ የኪነ ጥበብ ዕድገቷ ግን የዘመኑን ያህል ሳያድግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ኪነ ጥበብ ለሁለንተናዊ ብልፅግና ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር እንደሆነች መንግስት ፅኑ እምነት እንዳለው የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ ኪነ ጥበብ የትናንት፣ የዛሬንና የነገን ትውልድ በማስተሳሰር ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳላት አብራርተዋል። ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት አዲስ አበባ ከተማ በፈጣን የለውጥ ጉዞ ላይ እንደምትገኝ በመጥቀስ፤ ለነዋሪዎች ምቹ ለኪነ ጥበብ ደግሞ ዘመኑን የዋጀ የመከወኛ ሥፍራ እየሆነች መምጣቷንም በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ አስታውሰዋል፡፡
በተለይ ከንቲባዋ የተናገሩት አንዱ ጉዳይ፣ የጥበብ ስራ በአዳራሽ ብቻ የተወሰነ ባለመሆኑ እና ወደ ማህበረሰቡ ቀረብ እንዲል በከተማዋ በተተገበረዉ ሁለንተናዊ ለውጥ የተለያዩ የውጭ የኪነ ጥበብ ስራ የሚከወንባቸው 110 ፕላዛዎችና ከ50 በላይ አምፊ ቴአትር ማሳያዎች በከተማዋ መገንባታቸውን ተናግረዋል። ከሳምንት በፊት የተመረቀው የህፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስም ሁለት ባለ 14 ወለል ብሎኮችን፣ 1 ሺህ 200 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው አንድ ቴአትር እና ሁለት ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶች እንዲሁም ልዩ ልዩ መገልገያዎችን ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የባህል፣ የሰላምና ኪነ ጥበብ ተመራማሪው ወሰን ባዩ (ዶ/ር) በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ የቴአትርና ሲኒማ ቤቶች ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳላቸው ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል። የአንድ ሀገር ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች እንዲያድጉ ሲኒማ ቤቶችና የጥበብ መከወኛ ሥፍራዎች ቁልፍ ናቸው ያሉት ተመራማሪው፣ የኪነ ጥበብ ዕድገት ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ የእሴት መጎልበትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ የጥበብ ሥራዎችና ባህል ተያያዥ መሆናቸውን ያብራሩት ወሰን ባዩ (ዶ/ር)፣ የትውልዱን ሰብዕና በመቅረጽና በባህሉ የሚኮራ ዜጋ ለማፍራት መሰል የጥበብ ሥፍራዎች ግንባታ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፡፡ እንዲሁም አዲሱ ትውልድ ጥበባዊ ሥራዎችን እንዲወድድ፣ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያደንቅና ሀገራዊ እሴቶቹን እንዲገነዘብ የተገነቡት ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ስፍራዎች አስፈላጊ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው እና የኪነ ጥበብ ባለሙያው ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) ከሰሞኑ በመዲናዋ የተገነባውን ዘመናዊ የህጻናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ መመረቁን ተከትሎ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፣ ሀገራት የተሰሩት በትርክት ነው፤ ችግር ሲያጋጥማቸውም ከችግራቸው የሚወጡት በትርክት ነው፤ ይህ ትርክት ደግሞ የሚገለጸው በኪነ ጥበብ መሆኑን በማስታወስ በመዲናዋ የተገነቡ ቴአትርና ሲኒማ ቤቶች ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ስለ ሀገር የሚሰሩ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎችን ወደ ህዝብ ለማስረጽ ህዝባዊ ስፍራዎችን ማብዛት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በተለይ ሰሞኑን ተጠናቅቆ ለምርቃት የበቃው የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ማዕከል እጅግ ዘመናዊና ዘመኑን የዋጀ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ቴአትርና ፊልሞችን በመዲናዋ በሚገኙ ቴአትር ቤቶች ለዓመታት መመልከቱን ያጫወተን ጋዜጠኛ ገነነ ብርሃኑ፣ የሲኒማው ዓለም ከደረሰበት ደረጃ አንጻር የመዲናዋ ሲኒማ ቤቶች ትልቅ ክፍተት ነበራቸው ብሏል፡፡ ለአብነትም የሲኒማ ቤቶቹ የድምጽ ጥራት፣ የመብራት አጠቃቀም፣ ተመልካቹ አየር የሚቀበልባቸው ክፍት ስፍራዎች እጥረትና የሳቢነት ጉድለት እንደነበራቸው አጫውቶናል፡፡ በዓድዋ መታሰቢያ ሥር የተገነቡ ሲኒማ ቤቶችን ጨምሮ በመዲናዋ የተገነቡ ሌሎች የጥበብ ስፍራዎች የነበረውን ችግር መቅረፍ እንደሚችሉም ተናግሯል፡፡
ፍራንሲስ ሶካሪ የተባሉ የቴአትር ተመራማሪ “ADVANCEMENT AND EVOLVING APPROACHES TO THEATRE DESIGN IN THE 21st CENTURY” በሚል በመጋቢት 2023 አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አሳትመው ነበር፡፡ በዚህ ጥናታቸው የቴአትር ጥበብ ባለንበት ክፍለ ዘመን በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስፍረዋል፡፡ በተለይ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገት በጥበባዊ ስራዎች ላይ የማይታመኑ ለውጦችን እያስከተለ መሆኑንም ጥናታቸው አትቷል። ከዚህ አንጻር በመዲናዋ የተገነቡ ቴአትርና ሲኒማ ቤቶች ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ የጥበብ ሥራዎች ለመስራት እጅግ ወሳኝ ናቸው፡፡
ምክንያቱም ዘመናዊ የቴአትርና ሲኒማ ቤቶች ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ መገንባታቸው የኪነ ጥበብ ስራዎች ጥራት እንዲያድግ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ አዳዲስ ሲኒማ ቤቶች የድምፅ (Sound System) እና የብርሃን (Lighting System) ስርዓቶችን ጨምሮ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አቅም የተሟላላቸው በመሆናቸው፣ አርቲስቶች ከዚህ ቀደም የማይታሰቡ ውስብስብ እና አስደናቂ ትዕይንቶችን መድረክ ላይ እንዲያሳዩ ያስችላቸዋል።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለው የቴአትር ጥበብ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር እየተሳሰረ ይገኛል። ዘመናዊ ቴአትርና ሲኒማ ቤቶች በኮምፒዩተር የታገዘ ዲዛይን በመጠቀም የጥበብ መድረኩ ላይ መልከ ብዙ ትዕይንቶች እንዲታይ ማድረግ ችለዋል። ይህም ከነባር ሲኒማ ቤቶች በተለየ ዘመኑን የሚመስሉ አዳዲስ ሲኒማ ቤቶች መገንባት የድራማውን ትረካ ጥልቀት በመጨመር ለተመልካች አዲስ እና መሳጭ ትዕይንቶችን ይሰጣሉ፡፡ እንዲሁም ምቹ የመድረክ አቀማመጥ እና ከስክሪፕት ውጪ የሚደረጉ ፈጣን የትዕይንት ለውጦችን የሚፈቅዱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለመተግበር ስለሚያግዙ ከያኒያን የፈጠራ ወሰናቸውን እንዲያሰፉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ። ከዚህ አንጻር አዲስ አበባ ውስጥ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማሳያ ሥፍራዎች በተለይ እይታዊ ጥበባትን ወደ ሌላ እርከን ከፍ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል፡፡