የዘመናዊ ግብይት በር ከፋች

You are currently viewing የዘመናዊ ግብይት በር ከፋች

“የኮሪደር ልማቱ ለአዲስ አበባ የንግድ እንቅስቃሴ መዘመንና መሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል”

በአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ

መነሻዬን አምስት ኪሎ፤ ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ አድርጌ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ጉዞዬ ከስድስት ኪሎ ወደ 4 ኪሎ የሚወስደውን ዋና የአስፓልት መንገድ ከጀርባዬ ትቼ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም እና በቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን መካከል ባለው አማራጭ(ማስተንፈሻ) የአስፋልት መንገድ በመከተል ነበር። ይህ መንገድ እና አካባቢው በኮሪደር ልማት በመገንባት ላይ ነው፡፡ የግንባታው ሂደትም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ፤ በየዕለቱ የሚታየው ለውጥ ይመሰክራል። አንድ ሁለት እየተራመድኩ፤ ዙሪያ መለሱን ተመለከትኩ፤ ቃኘሁት፡፡ ከፊት ለፊት መሃል ፒያሳ በቅርበት ይታያል። የመሪ መዘጋጃ ቤቱን፣ የዓድዋ ሙዝየምን ጨምሮ ነባር እና በግንባታ ላይ ያሉ አዳዲስ ሕንፃዎች በጉልህ ይታያሉ፡፡ ወንዙና የወንዝ ዳርቻው እንደ በቆሎ እሸት ተገላልጦ ዓይንንም፤ ስሜትንም፣ ልብንም የሚያረካ ተፈጥሯዊ ምላሽን ያለስስት ይሰጣል፡፡ ሁሉም ነገር ደስ ይላል፡፡

አማራጩን (ማስተንፈሻ) መንገዱን ጨርሼ፤ ከፒያሳ ወደ 4 ኪሎ-መገናኛ የሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ደረስኩ። ወደ ግራ ታጠፍኩ፡፡ በተንጣለለው ምቹ የእግረኛ መንገድ የእግር ጉዞን እንደመረጡ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ዘና ብዬ መራመዴን ቀጠልኩ፡፡ የንግድ፣ የአገልግሎት፣ የፋይናንስ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሥራ ላይ ናቸው፡፡ ሰዓቱ ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ሆኗል። አየሩ ደስ ይላል። ባይደክመኝም አረፍ ማለት ፈለግሁ፡፡ አማራጭ አላጣሁም። ከኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ፊት ለፊት ከሚገኘው መናፈሻ ተቀመጥኩ፡፡ ቦታው በኮሪደር ልማቱ አዲስ ገፅታና ውበትን ተላብሶ፣ ለነዋሪው ማረፊያና የካፌ አገልግሎት እንዲሰጥ የተደረገ ነው። በዚህ ፓርክ እና በእግረኛ መንገዱ መካከል የአውቶብስ እና የታክሲ ፌርማታ(መጫኛና ማውረጃ) በመኖሩ፤ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ሲወርዱ ወይም ለመሳፈር ሲሰናዱ ይህንን ቦታ ያርፉበታል። ከካፌውም አገልግሎት በፍቃዳቸው  ይጠቀማሉ፡፡

ወጣት እስራኤል ካሳሁን እና ወጣት ኤርሚያስ ሰሎሞን በዚህ ሥፍራ ቁጭ ብለው፤ ሻይ ቡና እያሉ ሲጨዋወቱ ነው ያገኘኋቸው፡፡ መኖሪያቸው ቀበና አካባቢ እንደሆነ በመጠቆም፤ ትራንስፖርት ሳይጠቀሙ በእግራቸው መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡ የመጡበት ዋና ዓላማ መጽሐፍ ለመግዛት ሲሆን፤ በዚህ ሥፍራ እረፍት ወስደው ሻይ ቡና ማለትን የመረጡት የቦታው ገፅታና ምቹነት ስቧቸው እንደሆነ አልሸሸጉም፡፡ እንደዚህ ዓይነት አገልግሎቶች ተፈጥሯዊ ገፅታቸውን በጠበቀ መልኩ ከቤት ውጭ በተዝናኖትና በምቾት መጠቀም የሚያስችሉ በርካታ ቦታዎች በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸው በመልካምነት የሚጠቀስ ተግባር ነውም ብለዋል፡፡

የ4 ኪሎ ታክሲ ተርሚናልና ፕላዛ፤ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቃ የኮሪደር ልማቱ ሌላኛው ትሩፋት ነው፡፡ ተርሚናሉ በ5 ሺህ 480 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በውስጡ የገበያ ማዕከላት(ሱፐር ማርኬቶች)፣ ካፍቴሪያዎች፣ ኤቲ ኤም ማሽኖች፣ ጋዜጣ ማንበቢያና መሸጫ ሱቆች፣ ፣ መዝናኛ ቦታዎችና የኢንተርኔት መጠቀሚያ ዋይ ፋይ ያለው ነው፡፡ ከመሬት በላይ ብቻ ሳይሆን ከመሬት ውስጥም የንግድ እንቅስቃሴ ለማከናወን የሚያስችል ግንባታ ማከናወን እንደሚቻል በኮሪደር ልማቱ በተግባርም የታየበት ነው፤ ይህ ፕሮጀክት። ቀደም ሲል እግረኞችን ከትራፊክ አደጋ ለመጠበቅ ሲያገለግል የነበረው ድልድይ መሳይ መሸጋገሪያን በመሬት ውስጥ በተገነባ ዘመናዊ መሸጋገሪያ የለወጠው፤ በመንገድ ላይ ይዘወተር የነበረውን የሕገ ወጥ ንግድ ሥራ በመሬት ውስጥ እና ከመሬት በላይ በተገነቡ የንግድ ማዕከላትና ሱቆች ለሕጋዊ ነጋዴዎች ማመቻቸት የቻለው፤ የኮሪደር ልማቱ ነው፡፡

የ4 ኪሎ የገበያ ማዕከልና የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክት ለከተማ ነዋሪው አስፈላጊ የሚባሉ አገልግሎቶች በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በመቅረብ ላይ ናቸው፡፡ ኪዊንስን ጨምሮ የተለያዩ ትላልቅ የንግድ ተቋማት ምርታቸውን ለተጠቃሚው ማድረሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ የምግብ እና የመጠጥ አገልግሎት ሰጪዎችም ሥራቸውን በትጋት እያከናወኑ ነው፡፡ ስኬትን የመሳሰሉ የፋይናንስ ተቋማትም ቅርንጫፎቻቸውን በዚሁ ከፍተዋል። የጋዜጣና የመጽሔት አከፋፋዮች እና አስነባቢዎች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከተዘጋጀላቸው ሥፍራ ተሰይመው ነባሩን ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡

የሂክማ ቡና (Hikma Coffee) በ4 ኪሎ የገበያ ማዕከልና የመኪና ማቆሚያ ውስጥ አገልግሎታቸውን ከሚያቀርቡ የንግድ ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከመሬት በላይ ባለው የመጀመሪያ ወለል ላይ የሚገኘው ሂክማ ቡና ደንበኞችን በሚስብ ሁኔታ ተደራጅቷል፡፡ ኢትዮጵያዊ የቡና አፈላል ሥርዓትን የሚያሳይ ገፅታን ተላብሷል። ከተጠቃሚዎቹ መካከል አቶ ዑመር ኢድሪስ እና አቶ ጥላሁን ገብረእግዚአብሔር ይገኙበታል፡፡ ከአስር ዓመት የተሻገረ ጓደኝነትና ወዳጅነት ያላቸው ሲሆን፤ 4 ኪሎ ለእነሱ የሥራ ቦታቸው ብቻ ሳይሆን የትዝታቸው አንድ አካልም መሆኗን አንስተዋል። በ4 ኪሎ ሁሉም እንደሚገኝ በማስታወስ፤ ከነባሩ ገፅታ ጋር በተናበበ መልኩ በኮሪደር ልማቱ የተሠራው ሥራ ለአካባቢው አዲስ ውበትና ምቾት እንደጨመረለት መስክረዋል፡፡ “አሁን ባለንበት ሥፍራ ከዚህ ቀደም ቡና፣ ጁስ እና መሰል አገልግሎቶች ይሰጡ ነበር። አሁንም እነዚህ አገልግሎቶች አሉ፡፡ የአሁኑ ከቀደመው የሚለየው ደረጃውን በጠበቀ ሕንፃ፣ ለተጠቃሚ ምቾት በሚሰጥ ዘና ያለ ቦታ፣ በሚማርክ እና ጥሩ አየር በሚያስገኝ ሁኔታ እየቀረቡ ናቸው። በዚህም በጣም ደስተኛ ነን፡፡ ፍራፍሬ፣ የፍጆታ ምርቶች፣ አልባሳት፣ ጫማ፣ መዋቢያዎችን የፈለገ ከዚህ ያገኛል፡፡” በማለት፤ ያልተጓደለ አገልግሎትን በተዋበ እና ደረጃውን በጠበቀ ማዕከል ማግኘት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

ወጣት መስከረም ታዬ፤ በሂክማ ቡና በአስተናጋጅነት ትሠራለች። እኛም ወጣት መስከረምን ስለ ሥራው ጠይቀናት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥታናለች፡፡ “ወደዚህ በቅርቡ ነው የመጣነው፡፡ ሥራው ጥሩ የሚባል ነው። ብዙ ተጠቃሚዎችን ለማፍራት ጊዜ አልወሰደብንም፡፡ የቦታው ምቹነት፣ ተማሪዎች፣ የመንግስት ሠራተኞች እና ሌሎችም የሚውሉበት አካባቢ ስለሆነ ተጠቃሚዎች አሉን፡፡ እኛ ያለንበት ማዕከል ብዙ ሱቆች በመኖራቸው እነሱጋ የመጡ ሰዎችም ሻይ ቡና ለማለት ወደኛ ጎራ ይላሉ። በአጠቃላይ፤ እኛ ጥሩ ሥራ እየሠራን ነው፡፡”

“የኮሪደር ልማቱ፤ ለአዲስ አበባ የንግድ እንቅስቃሴ መዘመንና መሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል” የሚሉት የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ ናቸው። ይህንንም ሲያብራሩ፤ “የንግድ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ድርጅቶች) በአዲስ እንዲከፈቱ፣ ነባሮች ደግሞ ደረጃቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ዕድል ፈጥሯል፡፡ የንግድ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን በተመቻቸ ቦታ እንዲያቀርቡ፤ ሸማችና ተጠቃሚዎችም የሚፈልጉትን ምርት ወይም አገልግሎት ከሚመች ሥፍራ ለመሸመት እና ለመጠቀም አስችሏቸዋል፡፡”

የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አክለው እንደገለፁት፤ የኮሪደር ልማቱ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የገበያ ማዕከላት፣ ካፍቴሪያ እና የመዝናኛ ስፍራዎች ለአገልግሎት እንዲበቁ አግዟል፡፡ ለመሰረተ ልማት መሻሻልና ተደራሽነት ማደግ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። እግረኛ፣ የብስክሌት ተጠቃሚዎች እና የመኪና አሽከርከሪዎች  በነጻነት የሚንቀሳቀሱባቸው የመንገድ መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል፡፡ እግረኞች የሚያርፉባቸው፣ አሽከርካሪዎች መኪናዎቻቸውን የሚያቆሙባቸው ቦታዎች በመሟላታቸው ጊዜ ወስደው በንግድ ተቋማት የሚፈልጉትን መገብየት እና መጠቀም የሚችሉበት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ምሽቱን እንደቀን  ብርሃን የሚያጎናጽፉ የመንገድ መብራቶች በመተከላቸው  የንግድ እንቅስቃሴው በቀንና በምሽት የሚሰጥበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ ይህም ለነጋዴውና ለሸማቹ ጥሩ ዕድል  ፈጥሯል፡፡ ከተማዋም ተጨማሪ ገቢ እንድታገኝ አግዟል፡፡

አዲስ አበባን በብዙ መልኩ እያሻሻላት የሚገኘው የኮሪደር ልማት፤ በፓርኮቿ ላይ ያሳረፈው አሻራ ጉልህ ነው፡፡ እነዚህ ፓርኮቹ ውበትና መዝናኛ ብቻ አይደሉም። የንግድ ሥራዎች ማዕከልም ሆነዋል፡፡ ይህንን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብ  መዝናኛ  ቦታዎች  አስተዳደር  ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማ ተሰማ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ የከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት አንድ ማሳያ የኮሪደር ልማቱ፤    በከተማችን በአራቱም አቅጣጫ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ አዳዲስ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው።  በውስጣቸው  የልጆች መጫዎቻዎች፣ ፋውንቴኖች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ አረፍ ብለው ንፁህ አየር የሚያገኙባቸው ምቹ ስፍራዎች፣ የእግር መንገዶች፣ ካፍቴሪያዎች፣ የባህል አልባሳት እና ቁሳቁሶችን  መሸጫ ሱቆች  ወዘተ የያዙ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የከተማዋ ነዋሪዎችም ሆኑ እንግዶች ወደ ፓርኮቹ በመምጣት እየተገለገሉባቸው ይገኛሉ፡፡ 

የስማርት ሲቲ ንድፈ ሃሳባዊ ዕውቀትን በተግባር እየገለጠች ያለችው አዲስ አበባ፤ ሁሉን አቀፍ በሆነ የለውጥ ጉዞ ላይ ትገኛለች፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የንግድ ማዕከላትን ማስፋፋትና ለአገልግሎት ማብቃት የስማርት ከተማነት መገለጫ ተደርገው ከሚወሰዱ ተግባራት መካከል ይገኛል፡፡ ይህንንም ለማሳካት እስካሁን ከተሠራው በላይ፤ እየተሠሩ ያሉትና የሚሠሩት እንደሚበልጡ መገመት አያዳግትም። ለማሳያነት በመሃል ፒያሳ(ቀድሞ ዶሮ ማነቂያ ይባል በነበረው) ስፍራ እየተገነቡ ያሉትን ሦስት ግዙፍ እና ዘመናዊ ሞሎች እና አፓርትመንቶች መመልከት ይገባል። በከተማ አስተዳደሩ እና የግል ሴክተር አጋርነት እየተገነቡ ያሉት እነዚህ ሞሎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ሲበቁ እንደ ከተማ ገቢ ለማሳደግ፣ የስራ ዕድልን ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪን ለማስገኘት እና ሁሉን አይነት ግብይት ከአንድ ስፍራ ማከናወን የሚያስችል ዕድልን በመፍጠር እና ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ውጤት እንደሚያመጡ ከዚህ ቀደም የግንባታ ሂደታቸውን በቦታው በመገኘት የጎበኙት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

የንግድ ሥራ ለከተማ እና ለከተሜ ወሳኝ ናቸው፡፡ ስለዚህ፤ ጅምሩ እንዲጠናከር፣ ውጤቱም እንዲበዛና እንዲሰፋ ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል እንላለን፡፡ 

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review