“የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እና ምርት በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት እንዲፈጠር መንቀሳቀስ፤ ከሕግ ተጠያቂነት እስከ ፍቃድ
ክልከላ የደረሰ እርምጃ ያስከትላል”
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ
አቶ ኤርሚያስ የሺጥላ ይባላሉ፡፡ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ነዋሪ ናቸው፡፡ መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች ያደረገው የደመወዝ ማሻሻያ ወቅቱን የዋጀ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች፤ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ተደማምሮ በሀገራችን ያጋጠመው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት በርካቶችን ፈትኗል፡፡ እሳቸውም ለምግብ፣ ለትራንስፖርት እንዲሁም ለትምህርት ቤት ክፍያ የሚሆን ወጪ ለመሸፈን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበዳቸው በመምጣቱ አራት ልጆቻቸውን ከግል ወደ መንግስት ትምህርት ቤት እንዲዘዋወሩ አድርገዋል፡፡
ለመንግስት ሰራተኞች የተደረገው የደመወዝ ማሻሻያ ወቅቱን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም አተገባበሩ ላይ ስጋት እንዳላቸው አቶ ኤርምያስ ያነሳሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲኖሩ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ሸቀጦችን በመደበቅ ኑሮ እንዲወደድ የማድረግ ልምድ አላቸው፡፡ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግ ከሆነ ህገ ወጥነት አይኖርም፡፡ የተለመደውን አሰራር በሚሰብር አግባብ መንግስት ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ መንግስት ለሚከውነው ህግ የማስከበር ሂደትም ህዝብ ተባባሪ በመሆኑ ህገ ወጥነትን መከላከል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አለም ወልደ ስላሴ ለመንግስት ሰራተኞች የተደረገው የደመወዝ ማሻሻያ ተገቢነትን እንደሚጋሩት ይናገራሉ። ቤት በማከራየት የሚተዳደሩት እኚህ እናት በግቢያቸው ሶስት የመንግስት ሰራተኞች ይኖራሉ፡፡ ተከራዮቻቸውም በርከት ላሉ ዓመታት ቆይታ የማድረግ ልምድ አላቸው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሰበብ በአስባቡ የኪራይ ጭማሪ አለማድረጋቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ “እኔ የተጋነነ፤ የተከራዮችን አቅም ያላገናዘበ የቤት ኪራይ ጭማሪ አላደርግም፡፡ ሰው እየተቸገረ ማስጨነቅ ይከብደኛል፡፡” ሲሉ የተደረገው የደመወዝ ማሻሻያ ኑሯቸውን ለማሻሻል ታሳቢ የተደረገ በመሆኑ የተለየ ጭማሪ ማድረግ ፍትሐዊ ነው ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡
በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለመንግስት ሰራተኛ የደመወዝ ማሻሻያ ሲደረግ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ፡፡ ይሄ ተግባርም ሊታረምና ገደብ ሊበጅለት ይገባል የሚል እምነት አላቸው። ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ መልክ ያለው የኑሮ ውድነት በሀገራችን የራሱ የሆነ ጫና ፈጥሯል። በሸቀጥ እቃዎች ላይ ጭማሪዎችን ማስተዋል አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንደ መፍትሄ ብለው ወ/ሮ ዓለም ያስቀመጡት ምርቶችን ከሰንበት ገበያዎች መሸመት እንዲሁም የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ጥቆማ በማድረግ ለህግ አካላት ማሳወቅ እንደሚገባ ጭምር አስረድተዋል፡፡
አቶ ኑረዲን አወል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 በተለምዶ ብርጭቆ አዲስ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴ ነው፡፡ የተለያዩ ለምግብነት የሚያገለግሉ ፍጆታዎችን እንደ ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ሩዝ፣ ምስር፣ ተልባ፣ ዘይት እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን እንደ ኦሞ፣ በረኪና፣ ላርጎ፣ ዳይፐር እንዲሁም ሞዴስና መሰል እቃዎችን ለማህበረሰቡ ያቀርባል፡፡
ለመንግስት ሰራተኞች የተደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ተከትሎ የተለየ የዋጋ ጭማሪ እንደማያደርግም አቶ ኑረዲን ይናገራል፡፡ የተለያዩ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶችን ለማህበረሰቡ ምክንያታዊና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ማድረስ በመቻሉ በርካታ ደንበኞች አሉት፡፡ ከሌሎች ሱቆች በተለየ የ10 እና የ15 ብር ቅናሽ በተለያዩ ምርቶች ላይ የማድረግ ልምድ አለው፡፡ የሚሸጣቸውን የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶችን የዋጋ ዝርዝር በማስቀመጥ ግልፅ የሆነ የአሰራር ስርዓት ተከትሎ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡
እኛም የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶችን ከመርካቶ በምንረከብበት ወቅት የዋጋ ጭማሪ ያጋጥመናል፡፡ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ ትላንት የተገዛ እቃ ዛሬ ላይ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ አይቀርም፡፡ ይህንንም በመረዳት ወቅታዊ ገበያውን ታሳቢ ባደረገ አግባብ እንደሚሰራ ገልጿል። ለመንግስት ሰራተኛው የተደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ተከትሎ የተለየ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ በህግ የሚያስጠይቅ በመሆኑ ነጋዴዎች መልካም ስነ ምግባርን በመላበስ ህብረተሰቡን የማገልገል ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ምክሩን ለግሷል፡፡
የኢፌዲሪ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ከመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ሊፈፀሙ የሚችሉ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ መንግስት የሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ ያስተላለፈው ውሳኔ የሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያግዝ በጎ ተግባርና አዎንታዊ እርምጃ ነው፡፡ የደመወዝ ማሻሻያው ከሀገራችን ጠቅላላ ህዝብ ቁጥር ከ2 በመቶ የማይበልጠውን የመንግስት ሠራተኛ እንደሆነ እና የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል መንግስት ለህብረተሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ታስቦ የተደረገ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ2018 ዓ.ም ባወጣው መረጃ አስቀምጧል፡፡
ከዚህ በፊት ካለው ልምድ ለመገንዘብ እንደሚቻለው አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ ሕግና ስርዓትን ጠብቆ የሚሠራ መሆኑ የሚያስመሰግን ቢሆንም የተወሰኑ በአፍቅሮተ-ነዋይ የታወሩ ነጋዴዎች ለሠራተኛው ኑሮ ማሻሻያ የሚደረገውን የደመወዝ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሯሯጡ ተስተውለዋል።
እንደዚህ አይነት ኢ-ሞራላዊ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ ከንግድ ሥነ-ምግባርና ሞራል አኳያ ሲታይ አሳፋሪ ተግባር መሆኑ ታውቆ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 እና በንግድ ውድድርና የሸማች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 እንዲሁም በወንጀል ሕግ 1996 ተላልፎ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ በማንኛውም የንግድ እቃ እና አገልግሎት ግብይት ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ወይም ሰው ሰራሽ እጥረት ለመፍጠር ምርት የሚሰውሩ እና አላግባብ የሚያከማቹ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም በየደረጃው የሚገኝ የንግድ መዋቅር ከሚመለከታቸው የፍትህ እና የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ የገበያ ማረጋጋት፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በማጠናከር በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ የግብይት ሂደቱ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ጠቁሟል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት መስከረም 2018 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረገው የደመወዝ ማሻሻያ የመንግስት ሠራተኞችን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የደመወዝ ማሻሻያው የሠራተኞችን የመግዛት አቅም የሚያሳድግ፤ በሌላ በኩል ነጋዴው ወደ ገበያው ለፍጆታ የሚያቀርበው ምርት መጠን እንዲያድግ የሚያስችል ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለፃ፤ መላውን የማህበረሰብ ክፍል የሚነካ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እና ምርት በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት እንዲፈጠር መንቀሳቀስ፤ ከሕግ ተጠያቂነት እስከ ፍቃድ ክልከላ የደረሰ እርምጃ ያስከትላል። የህግ ጥሰቱን ለመከላከል ግንባር ቀደም ኃላፊነት ያለበት ሸማቹ ማህበረሰብ ነው። ሸማቹ በንግድ ቦታዎች በሚገበያይበት ወቅት ከተለጠፈ ዋጋ ውጭ የሚሸጡ ነጋዴዎችን ሲመለከት በ8588 ነፃ የስልክ መስመር በማሳወቅ መብቱን ማስከበር ይኖርበታል፡፡
የመስከረም ወር በርከት ያሉ በዓላት የተከበሩበት እና ለመንግስት ሰራተኞች የተደረገው የደመወዝ ማሻሻያ የሚተገበርበት እንደመሆኑ ቢሮው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ለመከላከል በቂ ዝግጅት ማድረጉን የቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ በ219 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች፣ በ5ቱ የገበያ ማዕከላት እንዲሁም 20 ባዛሮችን በመክፈት የተለያዩ የኢንዱስትሪና ግብርና ምርቶችን በማቅረብ የተረጋጋ ግብይት እንዲኖር፣ የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ንረትን የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማቃለል እንደተሰራ እና እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በከተማዋ ከ500 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ይገኛሉ፡፡ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት የንግድ ሕጉን ተከትለው እየሰሩ ነው። የተቀሩትን ህጋዊ መስመር ለማስያዝ ቢሮው እየሰራ ይገኛል፡፡ ህገ ወጥ ግብይትና የዋጋ ጭማሪ እንዳይፈጠር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በየጊዜው ክትትል በማድረግ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የገለፁት ወ/ሮ ሀቢባ፣ ከምርት አቅርቦት በተጨማሪም መጋዘን ውስጥ ክምችት እንዳይኖር ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ በተለይ ተቆጣጣሪ አካላት የደንብ ልብስ እንዲለብሱና የሚይዙት መታወቂያ ልዩ የመለያ ኮድ ወይም ባር ኮድ እንዲኖረው እየሰራ ስለመሆኑ አስታውቀዋል፡፡
ሸማቹ ማኅበረሰብ በግብይት ወቅት በግልጽ ከተለጠፈ የዋጋ ተመን ውጭ የሚሸጡ ነጋዴዎች ሲያጋጥሙት ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ መብቱን ማስከበር እንደሚገባው የቢሮ ኃላፊዋ አስገንዝበዋል፡፡ ከተጠቀሰው የዋጋ ዝርዝር በላይ የሚሸጥ ነጋዴን ንግድ ፍቃድ በመንጠቅ፣ በማሸግ እና በመሰረዝ ከንግድ ስርዓት እንዲወጣ የሚደረግበት አግባብ ስለመኖሩ ጭምር አስረድተዋል፡፡ ቢሮው በአዲሱ በጀት ዓመት 2018 ነጋዴው ማህበረሰብ የንግድ ሕጉን ተከትሎ እንዲሰራ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን