የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች ምንያህል ተሾመ ፊቱን ወደ ስልጠና አዙሯል፡፡
2005 ዓ.ም ላይ ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ስታልፍ ከቡድን አባልነት ባለፈ ከዋነኛ ተዋናዮቹ አንዱ የነበረው ምንያህል እድሜያቸው ከ7 እስከ 17 የሚሆኑ ታዳጊዎችን እያሰለጠነ ይገኛል፡፡
ምንያህል ተሾመ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለቀድሞ ለሀገር ባለውለታዎች ባዘጋጀው መድረክ ላይ ስልጠና ወስዶ የአሰልጣኝነት ጉዞውን እንደ ጀመረ አስታውቋል፡፡
ከደደቢት ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ማሸነፍ የቻለው ምንያህል ተሾመ ስልጠና የጀመረው በያዘነው ዓመት እንደሆነ ከ ኤ ኤም ኤን ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡
ከአጋሮቹ ጋር በመሆን እያሰለጠናቸው በሚገኙ ታዳጊዎች ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳየ የሚናገረው ምንያህል ቀድሞም ሀገራችን የተሰጥኦ ችግር የለባትም ብሏል፡፡
ትልቁ ችግር የማዘወተሪያ ስፍራ እጦት እንደነበር ይህም አሁን ላይ መንግስት በሰጠው ትኩረት ተቀርፏል ሲል ተናግሯል፡፡
የምንያህል ተሾመ ትልቁ አላማው የሚያሰለጥናቸው ታዳጊዎች በሀገራችን ላሉ ታላላቅ ክለቦች እንዲጫወቱ መንገዱን ማመቻቸት ነው፡፡
ለዚህ የሚያበቃቸውን ስንቅ ለመስጠት እንደተዘጋጀ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ወክለው ሲጫወቱ ማየት እንደሚፈልግ ጠቁሟል፡፡
ምንያህል ተሾመ ለፕሮጀክቱ መጠናከር ድጋፍ ለሚያደርጉለት በተለይ በአሜሪካ ሲአትል ያሉ የብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋቾችን አመስግኗል፡፡
በሌሎች ግዛቶች የሚኖሩ እና ሀሳቡን ደግፈው ለሚያበረታቱት ሁሉ እጅ የነሳው ምንያህል ቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን ሜዳ ያመቻቹለት ሃላፊዎችንም አመስግኗል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ