18ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ፣ “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ቃል ይከበራል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀኑን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሠንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር መንግሥትና ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ሥልጣን፣ ነፃነት፣ ዕድገትና ማሕበረሰባዊ ትስስር መፍጠሪያ መሣሪያ መሆኑን ገልጿል።
ሠንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ የታተመ የሀገራዊ አንድነትና ነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ እንደሆነ አመልክቷል።
የአንድነታችንና የሕብረታችን ማሳያ፣ ጀግኖች አያቶቻችን ወራሪዎችን በማሸነፍ ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነውን ሠንደቅ ዓላማ የሕይወት መስዋዕትን ከፍለው ለአዲሱ ትውልድ ማስረከባቸው በመግለጫው ተወስቷል።
ይህንኑ መሠረት በማድረግ ሠንደቅ ዓላማ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት የሚከበር ታላቅ ሀገራዊ በዓል መሆኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ክብርና ተገቢውን ከፍታ አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሀገራዊ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን ማስቀጠል፤ ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት በማጽናት የሀገሪቷን የዕድገት ከፍታ ማረጋገጥ ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝቧል።
የብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በሠንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 (በተሻሻለው) አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ መጀመሪያ ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ተደንግጓል።
በዚሁም መሰረት የሠንደቅ ዓላማ ቀን የዘንድሮው በፌዴራል፣ በክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደር ከተሞች ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር ተገናዝቦና የኢትዮጵያን ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራትና ማንሰራራት በሚያረጋግጡ ውይይቶች ታጅቦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በመላው ሀገሪቱ ይከበራል፡፡
የሠንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን የከፍታ ብሥራትና ሕዳሴ ለማረጋገጥ ለሀገር ክብርና ጥቅም ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በሠንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃሉን የሚያድስበት ዕለት መሆኑን ምክር ቤቱ መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡
በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኤምባሲዎችና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ላይ ሠንደቅ ዓላማ በመስቀልና በሠንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ የመፈፀም ሥነ-ስርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ጠቁሟል።