ከኔልሰን ማንዴላ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ያገኙ አፍሪካውያን

You are currently viewing ከኔልሰን ማንዴላ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ያገኙ አፍሪካውያን

AMN-ጥቅምት 1/2018 ዓ.ም

በ1901 የተጀመረው የኖቤል ሽልማት በአለም ላይ ሰላምን ለማስፈን ፣ በዴሞክራሲ ግንባታ ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር እና በተለያዩ የፈጠራ መስኮች ለተሳተፉ ሰዎች እውቅና እየሰጠ ቀጥሏል።

የዘንድሮው ዓመት የኖቤል የሰላም ሽልማት ለቬንዚዌላዊቷ ፖለቲከኛ ማሪያ ኮሪና ተሰጥቷል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአለም ላይ የተከሰቱ እና ሊከሰቱ የሚችሉ በርካታ ጦርነቶችን በማስቆም እውቅናው እንደሚገባቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢደመጡም እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቷል።

ባለፉት አስርተ አመታት ከአፍሪካ በርካታ የሰላም ሎሬቶች ከኖርዌው የሽልማት ተቋም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

አነዚህ ግለሰቦች በቆራጥ መሪነታቸው ዕርቅ ፣ ነጻነት እና ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን ወሳኝ እርምጃዎችን ተራምደዋል ።

ኔልሰን ማንዴላ ከአፓርታይድ ጋር ካደረጉት ትግል ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቀጣናዊ ሰላምን ለማስፈን እስካደረጉት ጥረት ድረስ ፤አሸናፊዎቹ አህጉሪቱ በግጭት መካከልም ሆና ውይይት እና ሰላማዊ አማራጭን ለማመላከት ያደረጉት እንቅስቃሴ ለሽልማት አብቅቷቸዋል።

የአፍሪካ የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች ከተለያየ አካባቢዎች ፣ የፖለቲካ ሥርዓት እና ታሪካዊ ወቅቶች የተገኙ ናቸው ።

የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተሸላሚ አልበርት ሉቱሊ ሲሆኑ በ1960 በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የአፓርታይድን ተቃውሞ በመምራት እውቅናው ተበርክቶላቸዋል።

እንደ ኔልሰን ማንዴላ እና ዴዝሞንድ ቱቱ ያሉ ታዋቂ ግለሰቦች ይህንን በማስቀጠል ሀገሪቱን ወደ እርቅ እና አካታች ዴሞክራሲ መርተዋል።

የአፍሪካውያን የሰላም ሎሬት ዝርዝር ሲቀጥል በ1978 ከእስራኤል ጋር ባካምፕ ዴቪድ የሰላም ስምምነት በመፈጸም እና በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም በማስፈን የግብጹ አንዋር ሳዳት ተሸልመዋል።

ኬንያዊቷ ዋንጋሪ ማታይ የአካባቢ ጥበቃ እና ዘላቂ ልማትን ለማስፈን ባደረጉት ጥረት በ2004 ሽልማቱን የተቀበሉ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሴት ናቸው ።

በምዕራብ አፍሪካ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እና ላይማህ ግቦዌ በሊቤሪያ በሰላም ግንባታ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ በማበረታታት የ2011 ሽልማትን ተጋርተዋል።

የቱኒዚያ ሀገራዊ ምክክር ከአረብ ጸደይ በኃላ ሀገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በመምራት እንደ ቡድን ተሸልሟል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ከ20 አመታት በላይ የዘለቀውን ውጥረት ወደ ሰላማዊ ግንኙነት በመቀየር በ2019 የሰላም ሎሬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ምንም እንኳን የአፍሪካ ተሸላሚዎች ቁጥር ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም የጋራ ተጽኖአቸው ግን ከፍተኛ ነው።

ከፀረ-አፓርታይድ እንቅስቃሴ እስከ መሰረታዊ የሰላም ንቅናቄዎች እና የአካባቢ ፍትህ፣ የአፍሪካ የኖቤል ተሸላሚዎች በችግር ጊዜ የጽናት እና የሰላም ምልክት ሆነው ቀጥለዋል።

በዳዊት በሪሁን

#አዲስሚዲያኔትዎርክ

#PMOEthiopia

#NobelPeacePrize

#peace

#Ethiopia

#addisababa

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review