መስከረም – 30/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ከቅርብ አመታት ወዲህ በብዛት አህጉር አቀፍ እና አለም አቀፍ ሁነቶችን ማስተናገድ ጀምራለች ።
ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከአፍሪካ ህብረት ጋር ተያይዞ ከሚኖሩ ሁነቶች በዘለለ አለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ብዙም የማታስተናግ ከተማ እንደነበረች ይታወቃል ።
ይሁን እንጂ መንግስት ለከተሞች እድገት ያለውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በመገንዘብ አዲስ አበባን በማስዋብ በከተማዋ የሚካሄዱ ሁነቶችን የምትመጥን ከተማ በማድረግ ውጥኑን አሳክቷል ።
ለዚህም ማሳያ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና በወንዞች ዳርቻ የተሰራው ልማት በግንባር ቀደምነት መጥቀስ ይቻላል ።
የእነዚህ ፕሮጀክቶች እውን መሆን አዲስ አበባ በ2017 በጀት አመት ብቻ ከ150 የሚበልጡ አህጉር አቀፍ አለም አቀፍ ሁነቶችን ማስተናገድ መቻሏን የእነዚህ ኘሮጀክቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው።
ይህንን ጉዳይ በተመለከት ኤ ኤም ኤን ዲጅታል የአዲስ አበባ አስተዳደር ቱሪዝም ኮምሽን ኮምሽነር ከሆኑት አቶ ሁንዴ ከበደ ጋር ቆይታ አድርጓል ።
አቶ ሁንዴ በመዲናዋ የተካሄዱትን ኮንፍረንሶች በተመለከተ ሲያስረዱ ፣ ከተማዋ ከ150 የሚበልጡ አህጉር አቀፍ እና አለም አቀፍ ሁነቶች ስታስተናግድ በታሪክም የመጀመሪያ መሆኑን በመጠቆም ነው ።
ከዚህ ቀደም በመዲናዋ የሚካሄዱ ኮንፍረንሶች ምናልባትም ከአፍሪካ ህብረት ጋር ተያይዞ የሚደረጉ እንደነበር አስታውሰዋል ።
እነዚህ ሁነቶችም በዓመት ከ12 የማይበልጡ እንደነበሩ ያስረዱት ኮሚሽነሩ፣ አሁን ይሄ ታሪክ ተቀይሮ ከ150 የሚልቁ ሁነቶችን ማስተናገድ መጀመሩ ትልቅ እምርታ እንደሆነ አስገንዝበዋል ።
ለዚህ መሰረት የጣሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና እንደ ሀገር የተሰሩ ትልልቅ መሰረተ ልማቶች መሆናቸውን አመላክተዋል ።
መሰረተ ልማቶቹ እነዚህን ሁነቶች መሸከም የሚችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ፣ ከተሰሩት ውስጥ የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጰያን ታሪክ ለቀጣይ ትውልድ ከማሸጋገር ባለፈ ለማይስ እና ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ነው ኮምሽነሩ ያስረዱት ።

ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር ትልልቅ ኮንፍረንሶች ወደ መዲናዋ እንዲመጡ ትልቅ እድል ከፍቷል ሲሉ አቶ ሁንዴ ገልፀዋል ።
አህጉር አቀፍ እና አለም አቀፍ ሁነቶች ለመከናወናቸው በዲፕሎማሲ ረገድ የተሰሩ ስራዎች ለዚህ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል ።
በከተማዋ የተከናወኑ ኮንፍረንስ ቱሪዝም በርካታ ቁጥር ያለው ተሳታፊ ወደ ከተማዋ እንዲመጣ ያስቻለና በኢኮኖሚው ላይ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል ።
ለአብነት ያነሱት በቅርቡ በከተማዋ የተከናወነው 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ከ25 ሺህ በላይ እንግዶች የተሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ከዚህ ባለፈም የአገልግሎት ዘርፉን ከማዘመን እና ከማበረታታት አንፃር ከፍተኛ እንደሆነና ይህም የግሉን ዘርፍ ከማነቃቃት አንፃር ጉልህ ሚና እንደነበረው ገልፀዋል ።
ከዚህ ባሻገር የከተማዋን መልካም ገፅታ ከመገንባት አኳያ ያለው ፋይዳ በጣም ትልቅ መሆኑን አቶ ሁንዴ ገልፀዋል ።
የከተማዋ የቱሪዝም መዳረሻዎች ፣ የተሰሩ ትልልቅ ልማቶች የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ከማነቃቃት አኳያ ከሌሎች ጊዜያት በተለየ ሁኔታ ሰፊ ልምዶች የተወሰደበት እንደነበር ኮምሽነሩ አስረድተዋል ፡፡
በሔለን ተስፋዬ