ሰንደቅ ዓላማን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው ያውለበለቡ አብሪ ከዋክብት

You are currently viewing ሰንደቅ ዓላማን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው ያውለበለቡ አብሪ ከዋክብት

AMN- ጥቅምት 2/2018 ዓ.ም

ሃገር እና ህዝብ በሰንደቅ ዓላማ ይወከላሉ ፡፡ ከዚህም ከፍ ሲል በዜጎች የዓለም አደባባይ ተሳትፎና ተግባራት በሚገኙ ዕውቅና ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ በማውለብለብ ከግለሰብ አልፎ የሃገር እና የህዝብ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል ወይንም ይወከላል ፡፡

ታዲያ የኢትዮጵያ ስም በተለያየ ጊዚያት በዓለም ህዝብ ዘንድ ታትሞ እንዲኖር ያደረጉ የዜጎች ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ ተግባራት በተለያዩ የዓለም መድረክ ተከናውነዋል እየተከናወኑም ይገኛሉ ፡፡

ከእነዚህ ሁነቶች መካከል አትሌቶች ፣ ተመራማሪዎች ፣ ሙዚቀኞች እና በሌሎች ዘርፎች ዕውቅናን ያገኙ ዜጎች ተጠቃሾች ናቸው ።

ብዙውን ጊዜ ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርጎ የማውለብለብ ተግባር የሚከናወነው በአትሌቲክስ በሚደረጉ ውድድሮች እና ተሳትፎ ሲሆን በዚህም ብሔራዊ ኩራትን ለመግለጽ ተችሏል ።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም መድረክ አሸንፈው ሜዳልያ ሲያገኙ ደስታቸውን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበቡ የማክበር ባህል አላቸው ይህም በዓለም ህዝብ ልብ ውስጥ እንድንገኝ አንዱ ምክኒያት ነው ።

በፈረንጆቹ 1960 በኦሊምፒክ ውድድር በባዶ እግሩ ማራቶን በማሸነፉ የሚታወቀው አበበ ቢቂላ፣ ደስታውን ይገልፅ የነበረው የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ በማውለብለብ ነው።

አንጋፋው የረጅም ርቀት ሯጭ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴም፣ በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ካሸነፈ እና አዳዲስ የዓለም ክብረ ወሰኖችን ካስመዘገበ በኋላ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ደስታውን የገለፀበት ክስተትና ሰንደቅ ዓላማ በብሄራዊ መዝሙር ታጅቦ በዓለም መድረክ ከፍ ሲል በዓይኑ ያቀረረው ዕንባ ዛሬም ድረስ በብዙዎች ዘንድ የማይረሳ ሃገር ክብር የተገለፀበት ሁነት ነበር።

ፈር ቀዳጅ የሆነችው የረጅም ርቀት ሯጭ እና የበርካታ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ በብዙ ድሎቿ በኋላ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጋ አውለብልባለች ።

የሶስት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷ የረጅም ርቀት ሯጭ ጥሩነሽ ዲባባ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በትከሻዋ ይዛ በማውለብለብ በርካታ ድሎችን አስመዝግባለች ።

ሙዚቀኞች እና ሌሎች አርቲስቶችም ለሃገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር ለመግለፅ ሰንደቅ ዓላማዋን በኩራት አውለብልበዋል።

ከአትሌቶች፣ ከሙዚቀኞች እና ከአርቲስቶች ባሻገር ሌሎች ታዋቂ ሰዎችም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እና ኢትዮጵያውያን በተሰማሩበት ስራ ለዓለም የድርሻቸውን ማበርከት እንደሚችሉ ያስመሰከሩት በሰንደቅ ዓላማቸው ጥላ ስር ሆነው ነው ።

በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶችም በውጤታቸው የሃገርን ስም አስጠርተዋል ።

በምርምር በደረሱበት ግኝት እና ባስመዘገቡት ውጤትም እውቅና ሲቸራቸው ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ አድርገው አውለብልበዋል ።

በእፅዋት ማባዛት እና ዘረመል ምርምር፣ ድርቅና ጥገኛ አረምን የሚቋቋም የማሽላ ዝርያዎችን በማልማት በፈረንጆቹ 2009 የዓለም የምግብ ሽልማት፣ በ2023 የዩኤስ ብሔራዊ የሳይንስ ሜዳሊያ ሽልማትን ያገኙት ገቢሳ ኤጄታ (ዶ/ር)፡ የሀገርን ስም እና ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ካደረጉ የሃገር ኩራት እንዱ ናቸው ።

ታዋቂው የአካባቢ ተሟጋች እና ሳይንቲስት ብዝሃ ህይወትን እና ማህበረሰቦችን በዘረመል ሀብታቸው ላይ ያላቸውን መብት በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ሚና የነበራቸው ሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር በዘርፉ ላበረከቱት አስተዋፅዖ ተሸላሚ በሆኑበት ወቅት የሀገርን ክብር እና ሰንደቅ ዓላማን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ካስቻሉ ኢትዮጵያውያን መካከል ተጠቃሽ ሆነው በታሪክ ሰፍረዋል ።

ከዚህም ባለፈ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዲያስፖራ አባላት በሀገራቸውን ላይ የሚቃጡ ያልተገባ የውጭ ሃገራት ጣልቃ ገብነት ለማውገዝ እንዲሁም ለሃገራቸው እና ለህዝባቸው ያላቸውን ድጋፍ ሲገልፁ ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርጎ በማውለብለብ ሃሳባቸውን ሲገልፁ ማየት ሰርክ ሆኗል ።

የመንግስት ባለስልጣናት፡በዲፕሎማሲያዊ ስብሰባዎች እና በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውለብልበዋል እያውለበለቡም ይገኛሉ ምክኒያቱም ሃገር እና ህዝብ በሰንደቅ ዓላማ ይወከላሉና ።

ሰንደቅ ዓላማ የሀገር እና የህዝብ ምልክት ነው፣ ዜጎች በስኬታቸው ደስታቸውን ለመግለፅ እንደሚያውለበልቡት ሁሉ፣ የሀገራቸው አርማ ለሆነው ሰንደቅ ዓላማ እስከ ህይወት መስዋዕትነትም ዋጋ ይከፍላሉ ።

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለ18ኛ ጊዜ “ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ሀሳብ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም ይከበራል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review