ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት እመርታዊ ስኬቶችን እያስመዘገበች የሚመጥናትን ከፍታ እየያዘች ትገኛለች። ለዘመናት የቁጭት እና እንጉርጉሮ ትርክት ምንጭ የነበረዉን ዓባይን ገርታ የኃይል እና ብርሃን ምንጭ አድርጋለች፡፡
በንጋት ኃይቅ በምግብ ሉዓላዊነቷ ላይ ጉልህ ሚና የሚጫወት የዓሣ ምርት ማግኘት ችላለች፤ ዐዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ደሴቶችንና ከተሞችን ፈጥራለች፡፡ የዓባይን የቁጭት ትርክት ወደ ድል እና አሸናፊነት ብስራት ቀይራለች፡፡
ተጨማሪ የኃይል ምንጮችን ከውኃ እስከ እንፋሎት፣ ከፀሐይ ብርሃን እስከ ኑውክሊየር ኃይል እና ነፋስ በመገንባት ላይ ናት፡፡ እነዚህ ሁሉ የሰንደቋን ከፍታ እና ተምሳሌትነት የሚያጎሉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከገጸ ምድር ባሸገር በከርሰ ምድር ያሉ ሀብቶቿን ወደመጠቀም ተሸጋግራለች፡፡ በተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት የታየዉን ስኬት ለማላቅ፣ በነዳጅ ዘይትም ለመድገም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምራለች፡፡ የግብርና ዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ የዐፈር ማዳበሪያ በራሷ ለማምረት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሳለች፡፡ ይህም የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ሥራ ይበልጥ የሚጠናክር ሆኗል።
የሕዝቧን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር ከቢሮ እስከ ግቢ በሚል ጀምራ፣ ከከተማ እስከ ገጠር ወደሚል ተሸጋግራለች፡፡ በአዲስ አበባ የተጀመረዉ የከተሞችን ገጽታ የመቀየር ንቅናቄ ዘመናዊነትን፣ የስማርት ሲቲ ጽንሰ ሐሳብን እና ሰውን ከተፈጥሮ የማስማማት ልምምድን ያስተዋወቀ ነው፡፡ ይህም የዲፕሎማሲ ማእከል የሆነችውን መዲናችንን በዓለማቀፍ ደረጃ ያላትን ገጽታ የሚያጎላ፣ የሰንደቃችንን ከፍታ የሚጨምር ነው፡፡

ከተማችንን የማዘመኑን ጅማሮ ወንዞቻችን በማከም የተፋሰሶችን ደኅንነት የሚያረጋግጥ ሆኗል፡፡ ከእንጦጦ ጀምሮ እየተሠራ ያለዉ የወንዞች ዳርቻ ልማት የአዋሽ ተፋሰስን ሥነ ምኅዳር ጭምር የሚያክም ለአካባቢ ጥበቃ አብነት ነው፡፡ የገጠር አኗኗር ዘይቤያችንን በማዘመን ኢትዮጵያን በበጎ የምትመሰል ሀገር የማድረግ ጥረታችንም ፍሬው እየታየ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የሰንደቃችንን በኩራት መውለብለብ የሚያጎሉ የትጋታችን ውጤቶች ናቸው፡፡
ዛሬ የምናከብረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በነፃነት ቀን የተገኘ አይደለም፤ ነፃ ሆኖ ለሌሎች ነፃነት ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የታየ የነፃነት ምልክት እንጅ፡፡ ነፃነቱን ለማስከበር ግን ቀደምቶቻችን ደም፣ ሥጋ እና ዐጥንት ገብረዋል፡፡ ኢትዮጵያን የዓለም የነፃነት ቀንዲል አድርገዉ አስረክበውናል፡፡
ዛሬም እንደትናንቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በደም እና በዐጥንት ለማስበር የቆረጡ ጀግኖች አሉን፡፡ በምድር፣ በአየር፣ በባሕር እና በሳይበር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር ሰንደቋ የነፃነት ተምሳትነቱ እንዲቀጥል የሚተጉ ጀግኖቻችን አሉ፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ቀንን የምናከብረዉ በሁሉም ግንባር፣ በሁሉም ዓውድ ስለኢትዮጵያ ዋጋ የሚከፍሉ ጀግኖቻችን በማመስገን፣ ሰንደቃችንም በክብር ከፍ አድርገን በማውለብለብ፣ ለላቀ ከፍታዉ እንደምንተጋ ቃል በመግባት ነው፡፡ የተጀመሩ ትልልቅ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክቶች ለማሳካት ደግሞ ያለስስት በጋራ መጣር፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ ማናቸዉንም ዋጋ መክፈል ከዜጎች ይጠበቃል፡፡
እንኳን ለሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳችሁ!
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ጥቅምት 3/2018 ዓ/ም