የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ

You are currently viewing የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ

AMN-ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም

የሀገር ሰንደቅ አላማን ከፍ አድርጎ ለማሳየት ስፖርት አቻ አይገኝለትም። በታላላቅ የስፖርት መድረኮች መካፈል ሀገርን ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ታድላለች።

በተለይ በሩጫው አለም ስሟ ተደጋግሞ ተነስቷል። ሰንደቋ ለመላዉ ዓለም ተዋውቋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አብዝተው በሚዘወተሩት እግርኳስ እና አትሌቲክስ ስፖርቶች መሰረት እንዲይዙ አሻራ ማስቀመጥ ችላለች። በአትሌቲክስ ብርቱ አትሌቶቿ በዓለም አደባባይ ያመጧቸው የከዚህ ቀደም ድሎች ከኢትዮጵያ አልፈው አህጉሪቱን ቀዳሚ አድርገዋል።

ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ ለጤንነቱ ሳይሰስት ማራቶንን በባዶ እግሩ ሮጦ ድል ሲያደርግ የተነሳችው ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም። ድሉ ለመላው ጥቁር አፍሪካውያን ፈር ቀዳጅ ስለነበር የአህጉሪቱም ስም ደግሞ ደጋግሞ ተነስቷል።

ሻምበል አበበ ቢቂላ በፅናት እና በወኔ ተፋልሞ ማራቶንን በባዶ እግር ለመሮጥ የወሰነው ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ሲል ነበር። ወታደር እንደመሆኑ የሰንደቅን ትርጉም በደንብ የተረዳው አትሌቱ በባዶ እግር መሮጥ ለእርሱ ተራ ነገር ነበር። እርሱ ለሀገሩ ሰንደቅ ሕይወቱን ለመስጠት የማይሳሳ ብርቱ ጀግና ስለነበር።

ለሀገሯ ብሎም ለአፍሪካ ገድል ፈፃሚ የሆነችው ፋጡማ ሮባም የኢትዮጵያ ባለውለታ ናት። እ ኤ አ 1996 በአታላንታ ኦሎምፒክ ያስመዘገበችው የማራቶን ድል የኢትዮጵያን ሰንድቅ አላማ በአሜሪካ ምድር ከፍ ብሎ እንዲታይ አድርጓል። ኢትዮጵያን በኩራት ያስጠራችው ፋጡም ከ29 አመት በፊት ያገኘችው የማራቶን ድሏ በርቀቱ ለአፍሪካ የመጀመሪያ ተብሎ ተመዝግቧል።

ደራርቱ ቱሉ ሌላኛዋ የሀገር እና የአህጉር ብርሃን ናት። እ ኤ አ 1992 የባርሴሎና ኦሎምፒክ ተካፍላ በ10ሺ ሜትር ያመጣችው ወርቅ ዘላለም የሚዘከር ታሪክ ተፅፎበታል።

በኦሎምፒክ የመጀመሪያውን ወርቅ ሜዳልያ ያመጣች ጥቁር አፍሪካዊት የሚለው ማዕረግ ለደራርቱም ፣ ለኢትዮጵያም ብሎም ለአፍሪካም በኩራት የሚነገር ድንቅ ታሪክ ሆኗል።

ደራርቱ ቱሉ ለሀገር ሰንደቅ አላማ መዋደቅ ትልቅ ክብር መሆኑን ባለማመንታት ሁሌም ባገኘችው አጋጣሚ ትናገራለች። በተግባርም አሳይታለች። ድል አድርጋ የሀገሯ ሰንደቅ ሲሰቀል ስታይ አምብታለች።ሀገሯን ከፍታው ላይ በማስቀመጧ የደስታዋን ጥግ በእንባ ገልፃለች።

ሀይሌ ገ/ስላሴ ሀገር መውደድን ሰንደቋን ማክበርን ምንኛ ኩራት እንዳለው ደጋግሞ ተናግሯል። በተሳተፈባቸው ውድድሮችም ሀገሩን አክብሮ አስከብሯታል።

በወርቃማ እግሮቹ እየተስፈነጠረ ቀዳሚነቱን በተደጋጋሚ ለማንም ሳያስነካ ሰንደቋን ከፍ አድርጓል።

ድሉን እንዳረጋገጠ የሀገሩን ሰንደቀን መፈለግ ሁሌም የሚያደርገው ተግባሩ ነበር። ሰንደቁን ካልያዘ ባዶነት ይሰማዋል። ከማንም በላይ ልቆ ለመገኘት ልምምድ የሰራው በውድድሩም ያለውን አቅሙን ሁሉ የሰጠው ለሰንደቁ ክብር ነው።

ሀይሌ ገ/ስላሴ ሀገሩን ቀዳሚ ያደረገው ሙሉ ጤነኛ ሆኖ ብቻ አይደለም። እ ኤ አ በ2000 የሲድኒ ኦሎምፒክ 10ሺ ሜትሩን የተወዳደረው የእግር ጣት ጉዳት እያለበት ነበር። ይህን ያደረገው ለሀገሩ ክብር ሲል እንደነበር በወቅቱ ተናግሯል።

ሰንደቋ በብሔራዊ መዝሙሯ ታጅቦ ሲሰቀል ከማየት የበለጠ ደስታ ለሀይሌ ከየትም ሊገኝ አይችልም።

ለዚህም ነው እ ኤ አ በ1996ቱ የአትላንታ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳልያውን አግኝቶ ሰንደቅ አላማው ሲሰቀል ፈቅሎ የወጣው የደስታ እንባ ከቁጥጥር ውጪ የሆነበት።

ለማሳያ አራት አትሌቶችን አነሳን እንጂ ኢትዮጵያ በበርካታ ብርቅዬ አትሌቶቿ በዓለም ፊት ቀዳሚ ሆና ታይታለች። ሰንደቋም ከፍ ብሎ ተውለብልቧል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review