3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል ፡፡
በጉባኤው የተለየዩ የምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች አንስተው በስራ ሃላፊዎች ምላሽ እየተሰጠባቸው ይገኛል ፡፡ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ህብረተሰቡ የከተማዋን መሰረተ ልማት ከጉዳት እንዲጠብቅ በዘላቂነት ምን እየተሰራ ነው ይገኝበታል ፡፡
ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ እና ማብራራያ የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሠርቪስ እና ሰው ሀብት ቢሮ ሀላፊ ጀማሉ ጀንበር /ዶ/ር/፤ የከተማዋን የልማት ስራዎች በአግባቡ ለመጠበቅ እና በማስተዳደሩ ረገድ የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑን እና ይህንንም በህግ ለማስደገፍ ህገ-ደንብ መውጣቱን ገልጸዋል።

በከተማ የተሰራው የልማት ስራ ለመጠበቅ ደንብ ቁጥር 182/2017 ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል። በከተማዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወንዞች የቆሻሻ መጣያ የነበረውን አመለካከት የቀየረ እና በዘላቂነት የሚከላከል ተቋም ተቋቁሟል፤ ስራውን ለማከናወን እንዲረዳውም የህግ ማእቀፍ መዘርጋቱን አንስተዋል ።
ህብረተሰቡ ስለ ከተማዋ ልማት አጠቃቀም ጥሩ ግንዛቤ እንዳለው እና በአግባቡ አየተገለገለበት እንደሚገኝ ሃላፊው ገልፀው፤ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ አጠቃቀምን እንደምሳሌ አንስተው አብራርተዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች መኖርያ ቦታዎቻቸውን እስከ ሀያ ሜትር ርቀት፤ ተቋማት ደግሞ እስከ ሀምሳ ሜትር ርቀት ማጽዳት እና መከባከብ እንደሚጠበቅባቸው በተዘጋጀው ደንብ መካተቱን አመላክተዋል።
በ-ፍሬሕይወት ብርሃኑ