የ2026ቱ ዓለም ዋንጫ የአፍሪካ አህጉር የማጣሪያ ጨዋታዎች ነገ ይጠናቀቃሉ፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 53 ሐገራትን በዘጠኝ ምድብ ከፋፍሎ ሲያወዳድር ቆይቷል፡፡
ከእነዚህ ሀገራት መካከል የተወሰኑት ያስመዘገቡት ስታድየም የፊፋን ዝቅተኛ መስፈርት ባለማሟላቱ በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወቱ ተገደዋል፡፡
በምድብ አንድ ከግብጽ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሴራሊዮን፣ ጊኒ ቢሳውና ጂቡቲ ጋር ተደልድላ ማጣሪያዋን ስታድርግ የቆየችው ኢትዮጵያ በራሷ ሜዳ ከማይጫወቱ ሐገራት ውስጥ አንዷ ናት፡፡
ሀገሪቱ በባለሜዳነት የገባችባቸውን ጨዋታዎች በተዋሰቻቸውና በተከራየቻቸው የሞሮኮና ሩዋንዳ ስታድየሞች ተጫውታለች፡፡ እዚሁ ምድብ ላይ የሚገኙት ጂቡቲና ሴራሊዮንም ሁሉንም ጨዋታዎቻቸውን በደጋፊዎቻቸው ፊት አልተጫወቱም፡፡ ቡርኪናፋሶም ብትሆን ዘግይታ ነው ወደ ሜዳዋ የተመለሰችው፡፡

ከምድብ ሁለት ጎረቤት ሀገር ሱዳን የፊፋን መስፈርት የሚያሟላ ስታድየም ባለማስመዝገቧ ሊቢያ ቤንጋዚ ላይ ተጫውታ አሳልፋለች፡፡ እዚሁ ምድብ ላይ የምትገኘው ደቡብ ሱዳን የጁባ ስታድጠየም ግንባታን በማጠናቀቋ ከሁለተኛ ጨዋታዋ በኋላ ወደ ሜዳዋ ተመልሳለች፡፡ ቀሪዎቹ አራት ሀገራት በሜዳቸው ተጫውተው ማጣሪያቸውን አጠናቀዋል፡፡
ምድብ ሶስት ላይ ከተፋለሙ ስድስት ሐገራት ሶስቱ ስደተኛ ናቸው፡፡ ሌሴቶ፣ ዚምባብዌና ቤኒን በደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳና ኮትዲቯር ላይ የሜዳ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ከምድብ አራት ኢስዋቲኒ ብቻ ናት በገለልተኛ ሜዳ ስትጫወት የነበረው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ስታድየምን ስትጠቀም የነበረችው ኢስዋቲኒ ከዘጠኝ ጨዋታዎች በሶስቱ አቻ ወጥታ ሶስት ነጥብ ብቻ ነው ያላት፡፡
ኤርትራ ራሷን ባገለለችበት ምድብ አምስት ኒጀር የሞሮኮ ማራካሽን ስትጠቀም ኮንጎ በበኩሏ የጎረቤቷን ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክን ሜዳ ተጠቅማለች፡፡

ምድብ ስድስት ላይ የሚገኙት የምስራቅ አፍሪካ ተወካዮቹ ኬንያና ብሩንዲ ማጣሪያቸውን በገለልተኛ ሜዳ ጀምረው በራሳቸው ሜዳ ጨርሰዋል፡፡
ሀገራቱ ከፊፋ የተሰጣቸውን አስተያየት በማረም ወደ መጨረሻ አካባቢ የተካሄዱ ማጣሪያዎቻቸውን ወደ ሜዳቸው መልሰዋል፡፡ ሲሸልስና ጋምቢያ ግን ሁሉንም የማጣሪያ ጨዋታዎቻቸውን ያከናወኑት በገለልተኛ ሜዳዎች ነው፡፡
ጊኒ እና ሶማሊያ በምድብ ሰባት በውሰትና ኪራይ የተለያዩ ሀገራት ስታድየሞችን ተጠቅመው ማጣሪያቸውን ያደረጉ ሀገራት ናቸው፡፡
ከምድብ ስምንት ናምቢያና ሳኦ ቶሜና ፕሪንስፔ እንዲሁም ከመጨረሻው ምድብ ዘጠኝ ቻድ ፣ መካከለኛው አፍሪካና ማዳጋስካር ደረጃውን የጠበቁ ስታድየሞች ባለማስመዝገባቸው በሌሎች ሀገራት ሜዳዎች የተጫወቱ ናቸው፡፡
በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ከተሳተፉ 53 ሐገራት መካከል 23ቱ ወይም በመቶኛ ሲሰላ 43 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆኑት ሀገራት ሙሉ በሙሉና በከፊል የተጫወቱት በገለልተኛ ሜዳ ነው፡፡
ካፍ እነዚህን ስደተኛ ሐገራት ወደ ሜዳቸው ለመመለስ መስፈርቱን ማሟላት ወይም ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ የሚጠበቅበት የቅርብ ጊዜ የቤት ስራ ይሆናል፡፡
በታምራት አበራ