የግብጽ የእኔ ብቻ ልጠቀም ባይነት ዘመን አብቅቶ በናይል ወንዝ ላይ በጋራ የመልማት አዲስ የትብብር ምዕራፍ ተከፍቷል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የአባይ ወንዝ ዙሪያ የምታደርጋቸውን ጠብ አጫሪ ንግግሮች በጽኑ አውግዟል።
ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች የብቸኛ ተጠቃሚነት አባዜ መጠመዷን እንደቀጠለችበት አመልክቷል።
የግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣን ሀገራቸው በናይል ተፋሰስ ሀገራት በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የውሃ ጉድጓድ መቆፈሪያ እና የዝናብ መሰበብሰቢያ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን ፕሮጀክቶችን በመገንባት ከአፍሪካ ጋር አጋርነቷን እያሳየች ነው ማለታቸው እውነተኛ የቀጣናዊ ትብብር ፍላጎት ማሳያ አለመሆኑንም ገልጿል።
እውነተኛ የአፍሪካ አጋርነት በውሃ ሀብቶች ፍትሃዊነት እና እኩልነትን በመጠቀም ማመንና የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የመልማት መብትን እውቅና መስጠትን የሚጠይቅ መሆኑንም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመላክቷል።
ግብጽ በናይል ወንዝ ጊዜው ያለፈበትን የታሪካዊ መብቶች እሳቤ የሙጥኝ ብላ መቀጣሏን ገልጾ፤ ይህም ዓለም አቀፍ ህግን ያላከበረና የተፋሰሱን ሀገራት ህጋዊ መብቶች ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን አብራርቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት የናይል ወንዝ የመልማት መብቷን በመጠቀም እያደገ የመጣውን የኢነርጂ እና የውሃ ፍላጎቶቿን ለመመለስ እያከናወነች ያለውን ስራ በየትኛውም አይነት ጫና እንደማታቆምና አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እና የናይል ቤዚን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ላይ ስታደርጋቸው የነበሩ ድርድሮች ታማኝነት የጎደላቸው እንደነበሩም ገልጿል።
የናይል ቤዚን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ብቸኛ የጋራ የውሃ ተጠቃሚነት ማዕቀፍ መሆኑንም አስረድቷል።
ኢትዮጵያ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁሌም ዝግጁ መሆኗንም ገልጿል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የመልማት መብት እና ቀጣናዊ ትብብር መገለጫ መሆኑንም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።
ማስፈራሪያዎችንና ከመሰረታዊ የትብብር እሳቤዎች ያፈነገጡ አካሄዶችን በማቆም ከሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ መከባበር እና ፍትሃዊ መርሆዎች አብሮ መስራት እንደሚገባ አመላክቷል።
ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዘላቂ አጠቃቀም ላይ ከተፋሰሱ አገራት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው ያረጋገጠው።