በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሁለት ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ገለፁ፡፡
3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡
በጉባኤው የተለያዩ የምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ጥያቄዎችና አስተያየቶች አቅርበዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር የገፅ ለገፅ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ውይይቶች ዜጎች የመልካም አስተዳደር፣ የአገልገሎት አሰጣጥና የልማት ተደራሽነትን በተመለከተ ያነሷቸውን ጥያቄዎች የምክር ቤት አባላት ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡
ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ስልጠና የወሰዱ ዜጎችን በአፋጣኝ ወደ ስራ ከማስገባት አንፃር እና የመስሪያ ቦታ እና የገበያ ትስስር ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራራያ የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ፣ በ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለ77ሺ 500 ለሚሆኑ ወጣቶች እና ሴቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዞ የተሰራ ሲሆን ከ96ሺ በላይ የስራ ዕድል በመፍጠር ከዕቅድ በላይ ማከናወን መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንፃር አምራቾችን በተለያዩ ኤግዚብሽኖች እና ሁነቶች እንዲሳተፉ በማድረግ በተሰራው ስራ ሁለት ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩን አቶ ጥራቱ አንስተዋል፡፡
ከመስሪያ ቦታዎች ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ የሰጡት አቶ ጥራቱ፣ በመጀመሪያ የሩብ ዓመት 996 የመስሪያ ቦታዎች ለአዳዲስ ስራ ፈጣሪዎች መሸጋገራቸውንና ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡
በያለው ጌታነህ