45ኛው የገልፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ (ጂአይቴክስ) በዱባይ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ተጀምሯል።
የአውደ ርዕዩ “የዳታ ማዕከላት በነገ ዲጂታል መሰረተ ልማቶች ግንባታ ውስጥ ያላቸው ቁልፍ ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው። በጂአይቴክስ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች እና ባለሀብቶች እየተሳተፉ እንደሚገኙ Pulse of Africa ሚዲያን ዋቢ አድርጎ ኢዜአ ዘግቧል።
በዓለም ላይ ግዙፍ ከሚባሉት የቴክኖሎጂ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ጀማሪ ስራ ፈጠራ ትዕይንቶች አንዱ በሆነው መድረክ ላይ ከ180 ሀገራት የተወጣጡ ከ6 ሺህ 500 በላይ አቅራቢዎች፣ 1 ሺህ 800 ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች እና 1 ሺህ 200 ባለሀብቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
ጂአይቴክስ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ ኢኖቬተሮች እና ተመራማሪዎችን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ነው።
ዓለም አቀፍ አውደ ርዕዩ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ሳይበር ደህንነት፣ የጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ኢኖቬሽን፣ የጤና እና ባዮ ቴክኖሎጂዎች፣ ኮሙኒኬሽን፣ ሮቦቲክስ፣ የቀጣዩ ትውልድ ቴክኖሎጂዎች፣ የኮምፒዩተር ስርዓቶች እና ማሽኖችን ጨምሮ በርካታ ዘርፎችን ይዟል።
እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም በሚቆየው ዓለም አቀፍ ሁነት በዋናነት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ መሰረት ያደረጉ ፈጠራዎች እንደሚቀርቡና በዘርፉ ላይ ትኩረት ያደረጉ ውይይቶች እንደሚካሄዱም ተመላክቷል።