የከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት ትልቁ ትኩረት የቤት ግንባታ እና የውሃ አቅርቦት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

You are currently viewing የከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት ትልቁ ትኩረት የቤት ግንባታ እና የውሃ አቅርቦት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

AMN – ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም

የከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት ትልቁ ትኩረት የቤት ግንባታ እና የውሃ አቅርቦት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡

3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡

በጉባኤውም ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ህዝቡ የኮሪደር ልማት ያመጣውን ጥቅም እንደተገነዘበና እንደወደደው በመግለፅ፣ የኮሪደር ልማት ያልደረሰባቸው አካባቢዎች አሉ ያሉት የምክር ቤት አባላት፣ የኮሪደር ልማት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ልማቱን ለማዳረስ የከተማ አስተዳደሩ ምን አቅዷል በሚል ላነሱት ጥያቄ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ በርካታ ፍላጎቶች ቢኖሩም ሥራው ዕቅድ፣ ከፍተኛ በጀት እና ተጨማሪ በርካታ ነገሮች የሚያስፈልገው በመሆኑ በተያዘው በጀት ዓመት የኮሪደር ልማት ተብሎ እንደ አዲስ የሚጀመር ሥራ እንደማይኖር ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

ከንቲባዋ በምላሻቸው የ2018 በጀት ዓመት ትልቁ ትኩረት የቤት ግንባታ እና የውሃ አቅርቦት መሆኑንና ይህም በምክር ቤት በጀት የጸደቀ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዋናው እና ትልቁ ትኩረት፤ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንደመሆኑ መጠንም በመዲናዋ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የተወሰኑ መንገዶች የትራፊክ ስታንዳርድን በጠበቀ መልኩ ታቅደው መስተካከል የሚችሉ ህዝብ የጠየቀባቸው መንገዶች እንዳሉም አንስተዋል፡፡

እነዚህ መንገዶች ሲሰሩም የኮሪደር ልማት ስታንዳርድ ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለጹት ከንቲባዋ፤ የእግረኛ፣ የብስክሌት እና የተሸከርካሪ መንገዶችን ያሟላ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

ይሁንና ሁሉንም በአንድ ጊዜ መጀመር እንደማይቻል የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ ከኡራኤል ወደ ቦሌ ቪአይፒ የሚያገናኘው መንገድ በዕቅድ እንደተያዘ እና በመሰራት ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review