የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን 44ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓለም አቀፍ መደበኛ ስብሰባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ጉባኤውን የቤተክርስቲያኗ ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከፍተዋል።
በጉባኤው ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ የቤተክርስቲያኗ የስራ ኃላፊዎች፣ አገልጋዮች እና የየአህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት እየተሳተፉ ነው።
በጉባኤው መክፈቻ መልዕክት ያስተላለፉት ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ዘመንና ጊዜ ሳይገድበን ስራዎቻችንን በጥበብ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
ቤተ-ክርሲቲያኗ ከውጭም ከውስጥም የሚገጥሟትን ፈተናዎች በጥበብ በመሻገር አገልግሎቶቻችንን ልንሰጥ ይገባል ሲሉም ነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያስገነዘቡት።
ፓትሪያርኩ የሰበካ ጉባኤው በየዓመቱ መሰብሰብ ብቻም ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ችግሮችን በመለየት መፍትሄ የሚሆኑ ውሳኔዎችን የሚያስተላልፍበት መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በበኩላቸው፣ የጎደለንን ፍቅር፣ ሰላም መተሳስሰብና አንድነት ለመመለስ መንፈሳዊ ሀብቶቻችንን ተጠቅመን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
44ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓለም አቀፍ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 04 እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።
በፍቃዱ መለሰ