በመድረኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና በትምህርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ክህሎቶች ለሀገራዊ ግቦችና ለአህጉራዊ የ2063 የልማት አጀንዳዎች መሳካት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ናቸው።
ኢትዮጵያ ለክህሎት ልማት በሰጠችው ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ነው ብለዋል።
ክህሎት መር የፖሊሲ እርምጃችን ወጣቶች ከስራ ፈላጊነት ወደ ስራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩ በማድረግ የስራ ፈጣሪነት ባህልን በንቃት እያስተዋወቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመራቂዎች የራሳቸውን ስራ እንዲጀምሩ እና እድገት እንዲያመጡ የሚያስፈልጋቸውን ስልጠና፣ ምክር እና የገንዘብ ድጋፍ እያመቻቸ መሆኑን አመላክተዋል።
በስልጠና ተቋማት እና በኢንዱስትሪዎች መካከል ያለውን ትብብር የማጠናከር ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው የየህዝባችንን አቅም ወደ ውጤታማ፣ አሳታፊ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ወደሆነ የሥራ ኃይል መለወጥ አለብን ብለዋል።
ክህሎት የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ማዕከል መሆኑን ተናግረዋል።

የክህሎት ልማት ለአሳታፊ ዕድገትና ለተገቢ የሥራ ዕድሎች ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የትግበራ ዕቅድ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
አባል ሀገራት ሀገራዊ ለውጦችን ከአህጉራዊ ፍላጎቶች ጋር ለማጣጣም በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የተሻለ፣ ፈጣን እና ይበልጥ አሳታፊ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ያለውን የለውጥ አቅም መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል።
የፖሊሲ ወጥነትን እና ቀጠናዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ መጠቆማቸዉ ተዘግቧል፡፡