ኢትዮጵያ ወደ ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የጀመረችው ጉዞ ተጨባጭ ሃብቷ ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑ ተገለፀ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ወደ ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የጀመረችው ጉዞ ተጨባጭ ሃብቷ ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑ ተገለፀ

AMN – ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከጥገኝነት ወደ ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የጀመረችው ጉዞ ተመጋጋቢ ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁር አቶ ዮሐንስ በቀል ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል ።

መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ለህዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ባቀረቡት ሪፖሪት እና የመንግስት የስራ አቅጣጫ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ኢትዮጵያ ከምርኮ ወደ ሉአላዊ ኢኮኖሚ ግንባታ እየተሸጋገረች እንደምትገኝ አመላክተው እንደነበር ይታወሳል።

የፕሬዝዳንቱን ኢኮኖሚያዊ ንግግሮች በተመለከተ አቶ ዮሐንስ ሲያስረዱ፤ በተለይም በብድር እና እርዳታ ምክንያት የሚመጡ ኢኮኖሚያዊ ምርኮዎች እንደነበሩ በመጥቀስ፣ ኢኮኖሚውን ከምርኮ ወደ ሉአላዊነት ማሸጋገር የሚቻለው እንደ ህዳሴ ግድብ አይነት ፕሮጀክቶች በመተግበር መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል።

ይህም ሉአላዊ ኢኮኖሚ ሲፈጠር ከልካይ እንዳይኖር ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ ፣ ጋዝ ወደ ማምረት መሸጋገሯ፣ የዚሁ ምርት ተረፈ ምርት ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ ግብአት እንዲሆን ማድረጉን፣ አፈር ማዳበሪያው ደግሞ ለግብርና ዘርፍ ከጥገኝነት የተላቀቀ ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤቶች፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ኢኮኖሚያዋን እየገነባች ያለችው በውስጥ የተፈጥሮ ሀብቷ በመሆኑ ከየትኛውም ጫና የተላቀቀ ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ እየገነባች ትገኛለች ብለዋል።

በአለም ተለዋዋጭ ይዘት ምክኒያት አብዛኛው የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ውስን ዘርፍ ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበር አስታውሰው ፣ የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከግብርና መር ዘርፍ ወደ ብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ መቀየሩ ተጨባጭ ሀብቷን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ እየገነባች እንድትሄድ ምክንያት መሆኑን አመላክተዋል ።

ይህንን መሰረት ያደረገ ፍኖተ ካርታ ከማክሮ ኢኮኖሚው ሪፎርም አላማ ጋር ተስማሚ አድርጎ ስርዓት ባለው መንገድ ተግባራዊ መደረጉ ከምርኮ ወደ ሉዓላዊ ኢኮኖሚ ስርዓት ለመገንባት እንደሚያግዝ ነው የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አቶ ዮሐንስ በቀል ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ የገለፁት ።

በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review