የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ልማት በዋና ዋና ዓለም አቀፍ ኢኒሼቲቮች ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ አረጋገጡ፡፡
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ ልዑክ ከዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር ተወያይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ እና ሌሎች የመንግስት ልዑካን በዓለም ባንክ-አይኤምኤፍ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ከዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ ጋር ውጤታማ ውይይት አካሂደዋል።
ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ወቅታዊ ፕሮጀክቶች እድገት እና ለወደፊት ትብብር ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱም የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፣ ለኢትዮጵያ የልማት ግቦች እውቅና በመስጠት የዓለም ባንክ ላደረገው ከፍተኛ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ከድህነት ለመውጣት እየተተገበሩ ያሉ የማሻሻያ ሥራዎችን በተመለከተ ወቅታዊ መረጃ የሰጡት ሚኒስትሩ፣ እነዚህን የማሻሻያ ሥራዎች ለማስቀጠል የዓለም ባንክ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል።
በግብርና ፣ በሰው ሀብት ልማት፣ በቀጣናዊ ውህደት እና መሠረተ ልማቶች ባሉ ዘርፎችም የሚደረገው ድጋፍ መጨመር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ ተግባራዊ በተደረገ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ግቦችን ማሳካትን ጨምሮ አጠቃላይ የተሃድሶ መርሃ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግ አስተዋፅዖ ላበረከተው ጠንካራ አመራር የኢትዮጵያ መንግስትን አመስግነዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ልማት በዋና ዋና ዓለም አቀፍ ኢኒሼቲቮች ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል፡፡
ይህም የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት ያለመውን ተልዕኮ ኢነርጂ 300 ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ፤ የገንዘብ እና የእሴት ሰንሰለቶችን ለማሻሻል እና የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ እና በየዓመቱ ወደ ሥራ ለሚገቡ ኢትዮጵያውያን ጥራት ያለው የስራ እድል በመፍጠር ላይ ያተኮረ የአካባቢ ማኑፋክቸሪንግ ተነሳሽነትን እንደሚያካትት ነው ያረጋገጡት።
ስብሰባው ለሀገሪቱ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ወሳኝ አንቀሳቃሽ የሆኑትን የኢትዮጵያ የተሃድሶ አጀንዳ እና የልማት መርሐ-ግብሮች በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፀሙ የሁሉም አጋሮች ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ትብብር ያለውን ወሳኝ ሚና በማጉላት ተጠናቋል።