በኦሮሚያ ክልል አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀትን ይበልጥ ውጤታማ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ

You are currently viewing በኦሮሚያ ክልል አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀትን ይበልጥ ውጤታማ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ

AMN – ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም

በኦሮሚያ ክልል በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ለገጠር ሕብረተሰብ በቅርበት እየተሰጠ ያለውን መንግስታዊ አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

በክልሉ አዲስ ለተደራጁ የቀበሌ መዋቅሮች 6 ሺህ 800 የሞተር ብስክሌቶች ተከፋፍለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ እንደተናገሩት፥የክልሉ መንግሥት በመዋቅሮቹ የሚሰጠውን የሕዝብ አገልግሎት ለማሳለጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

በተለይ የአገልግሎት አሰጣጡን የማዘመንና በቴክኖሎጂ የመደገፍ፣ቀልጣፋና ፍትሃዊ የማድረግ ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

በክልሉ የገጠሩ ሕብረተሰብ የተሻለ መንግስታዊ አገልግሎትን በቅርበት እንዲያገኝ የቀበሌ መዋቅር በማደራጀት ወደ ተግባር መግባቱን ያወሱት የክልሉ ፕሬዚዳንት፤ አደረጃጀቶቹ የተፈለገውን አገልግሎት በመስጠት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በተለይ አደረጃጀቱን በሰው ሃይል ማብቃትና በሎጂስቲክስ ማጠናከር ላይ በትኩረት እየሰራን ነው፥ ይህም ሕዝባችን የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ እያስቻለ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

6 ሺህ 800 የሞተር ብስክሌቶች ለቀበሌ መዋቅሩ ስናስረክብ ለሕብረተሰቡ ይበልጥ በቅርበት አገልግሎት ለመስጠት ነው ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

የሞተር ብስክሌቶቹ በቀበሌ መዋቅር የመንግሥት አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚሰራውን ሥራ የሚያግዙ በመሆኑ በአግባቡ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውሉ አስገንዝበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቶሎሣ ገደፋ በበኩላቸው፥አዲሱን የቀበሌ መዋቅር በሎጂስቲክስ ለማጠናከር የሞተር ብስክሌቶቹ ርክክብ መደረጉን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ኮምፒውተሮች፣ የጽሕፈት መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሳቁስ ለቀበሌው አደረጃጀት መከፋፈሉን አውስተው፥ በዛሬው ዕለት ደግሞ የሞተር ብስክሌቶች ተከፋፍለዋል ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review