የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ለሌሎች ሀገራት እንደ ምሳሌ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን የአይኤምኤፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ተናገሩ

You are currently viewing የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ለሌሎች ሀገራት እንደ ምሳሌ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን የአይኤምኤፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ተናገሩ

AMN – ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ለሌሎች ሀገራት እንደ ምሳሌ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን የአይኤምኤፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ናይጄል ክላርክ ተናግረዋል።

በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራው እና የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያካተተ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከአይኤምኤፍ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ እና ከአይኤምኤፍ የአፍሪካ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

ልኡካን ቡድኑ በአይኤምኤፍ በሚደገፈው እና ኢትዮጵያ በነደፈችው የሀገር በቀል ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጉ ተነግሯል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ ለማራመድ አይኤምኤፍ እያደረገ ያለውን ወሳኝ ድጋፍ አድንቀው፤ የሪፎርሙ አላማ የሀገሪቱን ሙሉ የኢኮኖሚ አቅም በመክፈት፣ የሥራ ዕድል መፍጠር እና የሁሉም ኢትዮጵያውያንን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ሚኒስትሩ የሪፎርሙን ሂደት አስመልክቶ ባደረጉት ማብራሪያ፤ የዋጋ ንረት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ፣ የወጭ ንግድ በተለይም የወርቅ ኤክስፖርት መጨመር፣ የመንግስት ገቢ አሰባሰብ መሻሻል እና በአጠቃላይ የንግድ ምህዳሩ ያሳየውን እድገት ተናግረዋል።

ከአፍሪካ ታላላቅ ኢኮኖሚዎች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ እድገቷ ጋር የሚመጣጠን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲደረግላት ጠይቀዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር ) በበኩላቸው፤ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ ስር በሂደት ላይ ባለው የዕዳ መዋቅር ማሻሻያ ድርድር ላይ የተገኘውን አዎንታዊ እድገት ለአይኤምኤፍ አስረድተዋል።

አይኤምኤፍ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት፣ የተሻሻለ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት እና ኢኮኖሚውን ለመክፈት በኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰዱ እርምጃዎችን አድንቆ ፤ የሪፎርሙን ፍጥነት ማስቀጠል አስፈላጊ እንደሆነ አሳስቧል ።

ም/ዋና ስራ አስፈፃሚው ናይጄል ክላርክ አይኤምኤፍ የኢትዮጵያን ለውጥ ለመደገፍ የገባውን ቃል እንደሚያከብር ገልፀው፤ ተጨማሪ ፋይናንስ ለማሰባሰብ ከዓለም ባንክ ጋር በመሰራት ላይ ያሉ የልማት አጋሮች ጋር ቀጣይነት ያለው ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ም/ዋና ስራ አስፈፃሚው በታህሳስ ወር በኢትዮጵያ ለማድረግ ባሰቡት ጉብኝት፤ ከመንግሥት ተቋማት፣ ከፖሊሲ አውጪዎች እና ከግል ዘርፉ ጋር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review