አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በድሬዳዋ በመገኘት ከአስተዳደሩ ከንቲባ እና ሌሎችም አመራሮች ጋር በመሆን የድሬደዋን የኢንቨስትመንት አማራጮችና መሠረተ ልማት ስራዎች ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
ከጉብኝቱም በኋላ ከንቲባ ከድር ጁሃር እና ካቢኔያቸው ጋር የተወያየ ሲሆን የድሬደዋን መሠረተ ልማት አቅርቦትና የልማት አማራጮች አድንቋል።
የነፃ ንግድ ቀጠና፣ የደረቅ ወደብ እና የኮንቬንሽን ማዕከል ኢንቨስትመንትን ለመጀመር ሳቢ መሆናቸውን አንስቶ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎትና ዝግጁነት ያለው መሆኑን ኃይሌ አረጋግጧል።
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የልማት እንቅስቃሴ ከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማእከል ለማድረግ የሚያስችል እንዲሁም በሆቴልና መስተንግዶ ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ አመቺ ነው ሲልም አክሏል።
ድሬዳዋን የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እና የቱሪዝም ኮንፈረንስ ከተማ ለማድረግ በከተማው የተጀመሩ ስራዎች ኢንቨስት ለማድረግ ስለሚያመቹ ሌሎች ባለሃብቶችም በዘርፉ እንዲሰማሩ ምክረ ሀሳቡን ማጋራቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከተማዋ በጎብኚዎች ተመራጭ የሚያደርጋት የአየር ንብረት እና የተፈጥሮ ጸጋን የታደለች መሆኗን ገልፆ ይህም ለሆቴል ኢንቨስትመንቱ መሳካት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም አመልክቷል።