የ70 ዓመቱ ጣሊያናዊ የቪንሴንዛ ግዛት ነዋሪ ላለፉት 50 ዓመታት ሙሉ ማየት የተሳነው የአካል ጉዳተኛ በመምሰል ህዝብን በማታለሉ ክስ ተመሰረተበት።
አይነስውር በመምሰል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጥ የድጎማ ገንዘብ መሰብሰቡም ተረጋግጧል።
ግለሰቡ ላለፉት 53 ዓመታት ሙሉ በሙሉ ዓይነ ስውር ተደርጎ በአካል ጉዳተኞች ስም ድጎማ ሲቀበል የኖረ ሲሆን፣ አሁን ላይ አካል ጉዳተኛ አለመሆኑ ሊደረስበት በመቻሉ ክስ ተመስርቶበታል።
የቪንሴንዛ የፋይናንስ ፖሊስ ከአምስት አስርተ አመታት በኋላ በገባው ጥርጣሬ ግለሰቡን ለመከታተል እና መረጃዎችን ለመሰብሰብ ጥረት ማድረግ ይጀምራል።
በዚህም ግለሰቡ በገበያ ስፍራዎች የተለያዩ ቁሳቁሶችን እያገላበጠ ሲፈትሽ እንዲሁም በመኖርያ ቤቱ የአበባ ስፍራ ለአይነ ስውር ሰው ሊከብዱ የሚችሉ መሳሪያዎችን በመጠቀም ቁፋሮ ሲያከናውን እና አትክልት ሲተክል በቪድዮ እይታ ውስጥ ወድቋል።
ፖሊስ ዓይነ ስውር እንዳልነበረ የሚያሳይ ማስረጃ ለማሰባሰብ ለሁለት ወራት ባደረገው ክትትል፤ ግለሰቡ በከተማ ውስጥ ያለ ምንም ችግር ሲንቀሳቀስ ፣ የተለያዩ ግዢዎችን ሲፈፅም ፣ በርካታ ምርቶችን በአይን ሲመረምር እና ያለ ምንም እርዳታ በጥሬ ገንዘብ ሲከፍል ደርሶበታል።
ይህን ተከትሎም በመንግስት ላይ በፈጸመው የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥሮ በቪሴንዛ አቃቤ ህግ ቢሮ ክስ ተመስርቶበታል።
በአሁኑ ሰዓት ለግለሰቡ የሚደረጉ ሁሉም የበጎ አድራጎት ድጋፍ እና የማህበራዊ ዋስትና ጥቅማጥቅሞቹ በአስቸኳይ እንዲታገዱ መደረጋቸውን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
በመጨረሻም ባለፉት ዓመታት ተከሳሹ አላግባብ ከተቀበለው ገቢ ጋር የሚመጣጠን ከ200 ሺህ ዩሮ ታክስ እንዲከፍል እና የታክስ ኦዲት እንዲደረግበትም ታዟል።
በወርቅነህ አቢዮ