ኢትዮጵያ ልትገነባው ያሰበችው የኒውክሌር ሀይል ማመንጫ የሚሰጣቸው ጥቅሞች ምንድን ናቸው ?

You are currently viewing ኢትዮጵያ ልትገነባው ያሰበችው የኒውክሌር ሀይል ማመንጫ የሚሰጣቸው ጥቅሞች ምንድን ናቸው ?

AMN – ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም

የኒውክሌር ኃይል አብዛኛውን ጊዜ ከጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያዎች ጋር ተያይዞ የሚጠቀስ ቢሆንም፤ በዘመናችን ለሰላማዊ ዓላማዎች በስፋት እየዋለ ያለ ጠቃሚ የኃይል ምንጭ ነው።

ቴክኖሎጂው በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በኤሌክትሪክ፣ በኢንደስትሪ፣ በህዋ ሳይንስ ምርምር፣ በውሃ ማጣራት እና በሌሎችም ዘርፎች በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሀገራት በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ ይፋ ካደረጓቸው የ30 ቢሊየን ዶላር ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ለሰላማዊ አላማ የሚውል የኒውክሌር ማብላያ መገንባት ይገኘበታል።

የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ (ኒውክሌር ፕላንት) ኃይል ለማምረት ‘ዩራኒየም-235’ የተባለውን ንጥረ ነገር ይጠቀማል።

ከ1950ዎቹ ጀምሮ በዓለም ላይ በስፋት አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኒውክሌር ሀይል የአየር ንብረት ሁኔታ ሳይበግረው በቀን ለ24 ሰዓታት ኃይል ማመንጨት መቻሉ ተመራጭ ያደርገዋል። ከድንጋይ ከሰል አልያም ከጋዝ የሀይል ማመንጫ ጣብያዎች በተሻለ የኒውክሌር ፕላንት በጥንቃቄ ከተያዘ 80 እና ከዛ በላይ አመታትን ማገልገል ይችላል።

በትንሽ ቦታ በጥቂት ግብአት ትልቅ ሀይል ማመንጨት መቻሉ ተመራጭ እንዲሆን ያስቻለው ነጥብ ነው።

ለአብነት በአንድ ኪሎ ግራም ዩራኒየም የሚመረት የኒውክሌር ኃይል በዲንጋይ ከሰል ከሚመረተው ኃይል በ20 ሺህ እጥፍ የሚበልጥ ስለመሆኑ ከአለም አቶሚክ ኢነርጂ ኤጂንሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ ከኤሌክትሪክ ኃይል ባለፈ በ32 ሀገራት ለተለያየ አገልግሎቶች የሚውሉ 440 የኒውክሌር ሀይል ማመንጫዎች ሲኖሩ 9 በመቶ የአለም ኤሌክትሪክ አቅርቦት ሽፋንም የሚገኘው ከነዚሁ ማመንጫዎች ነው።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ልትገነባው ያሰበችው የኒውክሌር ሀይል ማመንጫ የሚሰጣቸው ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ኒውክሌርን በውድ ዋጋ እየገዛችም ቢሆን እየተጠቀመችበት እንደምትገኘ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሸን ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

በህክምናው ዘርፍ የካንሰር በሽታን ለማከም፤ በግብርናው ዘርፍ የገንዲ በሽታ አምጪ የሆነውን የቆላ ዝንብን ለማምከን፣ እየተጠቀመችበት ትገኛለች።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በውሃ ላይ ጥገኛ ከሆነው የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት በተጨማሪ ከኒውክሌር ለማመንጨት እየተዘጋጀች ነው።

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ስምምነቶችን የፈረመች ሲሆን፤ ስምምነቱ የኒውክሌር ኃይልን በስፋት በሚጠቀሙና ለመጠቀም ፍላጎት ባላቸው አገራት የኒውክሌር ቁሳቁሶች አጠቃቀም፣ ለሰላማዊ አገልግሎት መዋላቸውን ለማረጋገጥ በአጠቃላይ የአጠቃቀም ስምምነቶች በተቀመጡበት አግባብ መፈጸማቸውን የማረጋገጥ ግዴታ የሚጥልነው።

ሰላማዊ የኒውክሌር አማራጭ በአሁኑ ወቅት ከኤሌክትሪክ ባለፈ በአለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝባቸው 4 ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?

  1. ህክምና

የኒውክሌር ቴክኖሎጂ በህክምናው ዘርፍ ትልቅ አብዮት አምጥቷል ራዲዮቴራፒ የተባለው ህክምና የካንሰር ሴሎችን ለመግደል ከፍተኛ ኃይል ያላቸውን ጨረሮች የሚለቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሽታውን ለመዋጋት ሁነኛ አማራጭ እንደሆነ ይነገርለታል። የሰውነትን የውስጥ አካላትን ለመቃኘት እና በሽታዎችን ለመለየት የሚውለው ራዲዮአክቲቭ አይሶቶፕስ የመሳሰሉ የስካን መሳሪያዎች የሚንቀሳቀሱት በኒውክሌር ነው።

ሆስፒታሎች የቀዶ ጥገና መሳሪያዎችን እና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችን ከባክቴሪያ እና ከሌሎች ተሃዋስያን ለማፅዳት ይጠቀማሉ፤ በእነኚህ እና በሌሎች የህክምና አገልግሎቶች እንዲሁም ምርምሮች ላይ ኒውክሌር ሰፊ ጥቅም ይሰጣል።

  1. ግብርና

የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ለምግብ ምርት መጨመርና ደህንነት በሚያደርገው አስተዋጽኦ ተጠቃሽ ነው።

ሰብልን ማበልጸግ (Crop breeding)፣ የሰብል ዝርያዎችን በማሻሻል፣ በሽታን እና ድርቅን የሚቋቋሙ፣ እንዲሁም የተሻለ ምርት የሚሰጡ አዳዲስ ዝርያዎችን ለመፍጠር የጨረር ቴክኒክ ጥቅም ላይ ይውላል።

ሰብል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ እና የምርት አቅምን የሚቀንሱ ነፍሳት እና ተባዮችን በመቆጣጠር ረገድ ያለው ሚና ደግሞ ሌላኛው አገልግሎቱ ነው። አርቴፊሻል በሆነ መንገድ የወንድ ተባዮች (ለምሳሌ የዝንብ ዝርያዎች) በመለየት እንዲጸዱ መራባት እንዳይችሉ እና ቀስ በቀስ ቁጥራቸው እንዲቀንስ ለማድረግ ይውላል።

  1. በምግብ እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ

ጨረርን በመጠቀም ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችን እና ሌሎች ምግቦችን ለረጅም ጊዜ እንዳይበላሹ ተሃዋስያንን ለመግደል ያገለግላል ይህም የምግብ ብክነትን ለመቀነስ ይረዳል።

ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች በየትኛውም ሁኔታ የማይቆራረጥ ሀይል እንዲያገኙ እና በኢንዱስትሪዎቻቸው ውስጥ ለሚያንቀሳቅሷቸው ማሸኖች የተለያዩ ጥቅሞችን ይሰጣል።

የቧንቧ ዝርጋታ፣ ድልድዮች እና የአውሮፕላን ክፍሎች ላይ ያሉ ስንጥቆችን ወይም ጉድለቶችን ለመለየት ጋማግራፊ እና ራዲዮግራፊ የሚባሉ የኒውክሌር ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ።

  1. በውሃ ሀብት እና በአካባቢ ጥናት

የውሃ ምንጭን ለመፈለግ የከርሰ ምድር ውሃ እንቅስቃሴን እና መጠኑን ለመለየት ራዲዮአክቲቭ ቀዳሚ አማራጭ ነው።

ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተገናኘ የብክለት ምንጮችን እና ስርጭታቸውን ለማወቅ በራዲዮአክቲቭ አይሶቶፕስ የአየር ወይም የውሃ ብክለቶችን ለመከታተል ያስቻላል።

ኢትዮጵያ በእድገት ግስጋሴ ላይ የሚገኘው ምጣኔ ሀብቷን ፍጥነት ለማስቀጠል የኒውክሌር ሀይል ማብላያዎችን ለመገንባት ወጥናለች።

ይህ የኒውክሌር ማብላያ ከሀይል አማራጭነት ባለፈ ለሁለገብ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚኖረው ትሩፋትም ከፍተኛ ነው።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review