ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ያገኘቻቸውን ውጤቶች በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ መድረክ ላይ አቅርባለች።
45ኛው የገልፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ (ጂአይቴክስ) በዓለም የንግድ ከተማ በሆነችው ዱባይ እየተካሄደ ይገኛል።
ይህ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ ኢኖቬተሮች እና ተመራማሪዎችን በአንድ መድረክ ያገናኘ የ2025 ጂአይቴክስ መድረክ በተለይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የሳይበር ደህንነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ውይይቶችም እየተደረጉበት ነው፡ ፡
ዛሬ በተካሄደው እና ትኩረቱን የመንግስትና የግል ተቋማት ትብብር ላይ ባደረገው ውይይት ኢትዮጵያም ተሞክሮዋን አካፍላለች።
ከግሪክ፣ ኦማን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬት የተሳተፉበት የዘርፉ ተወካዮች ጋር ተጋብዘው ንግግር ያደረጉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል ጉታ ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ያደረገቻቸውን ጥረቶች አስረድተዋል።
አቶ ዳንኤል በማብራሪያቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በሚል የሀገሪቱን የዲጂታል ዘርፍ ለማሳደግ ሰፊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እንደተከናወኑ ገልጸዋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ53 ሚሊዮን በላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ የዘርፉ እድገት ዜጎች የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አንስተዋል።
አቶ ዳንኤል በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ ዲጂታል ዘርፍ በፍጥነት እያደገ ከመሆኑ ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት አዳዲስ ፖሊሲዎችንና አሰራሮችን በፍጥነት ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በተለይ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚሰሩበት ህብር የተሰኘ አሰራር መዘርጋቱን ነው የገለጹት።
ህብር በሳይበር ደህንነት ላይ የሚሰሩ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ የሳይበር ደህንነት አገልግሎት የሚፈልጉ ተቋማት እንዲሁም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በጋራ እየሰሩ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ከመድረኩ በኋላ ከPulse Of Africa ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል ጉታ ኢትዮጵያ ዱባይ ላይ እየተካሄደ በሚገኘው የ2025 ጂአይቴክስ መድረክ ላይ መሳተፏ ሀገሪቷ በተለይ በቴክኖሎጂ፣ በሳይበር ደህንነት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ስማርት ሲቲ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ እየሰራች ያለውን ውጤታማ ስራ ለማሳደግ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በ2025 ጂአይቴክስ ዱባይ ከ180 ሀገራት የተወጣጡ ከ6 ሺህ 500 በላይ አቅራቢዎች፣ ከ1 ሺህ 800 በለይ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች እና ከ1 ሺህ 200 በላይ ባለሀብቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ከጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እየተካሄደ በሚገኘው አውደ ርዕይ በተለይ ከሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ጋር የተገናኙ ፈጠራዎች እና አገልግሎቶች በስፋት እየተዋወቁ ይገኛል።
በተጨማሪም የጤና እና ባዮ ቴክኖሎጂዎች፣ ኮሙኒኬሽን፣ ሮቦቲክስ፣ የቀጣዩ ትውልድ ቴክኖሎጂዎ እና ሌሎች በርካታ ፈጠራዎች ለእይታ መቅረባቸውን የPulse Of Africa ሚዲያ መረጃ ያመለክታል።