የአዲስ አበባ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በወንዞችና የወንዝ ዳርቻ በካይ ቆሻሻና ኬሚካል የለቀቁ ድርጅቶችና ግለሰቦችን መቅጣቱ አስታወቀ።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ኢትዮ ሌዘር ፋብረኢካ ኬሚካል ፍሳሽ ወደ ወንዝ በመልቀቅ 800ሺህ ብር ሲቀጣ 8 የመኖሪያ ቤትና 1 ድርጅት ደግሞ ባመነጩት ቆሻሻ አወጋገዳቸው ደንብን ተላልፈዉ ወንዞችን በመበከላቸው በድምሩ 592 ሺህ ብር መቀጣታቸዉን ባለስልጣኑ አስታዉቋል።
በተጨማሪም በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ረጲ ኮምዶሚኒዮም እና ግራር ሆቴል ፍሳሽ ቆሻሻን ከወንዝ በማገናኘታቸው በድምሩ 600ሺህ ብር፤ በቂርቆስ ክ/ከተማ ዲሊኦፖል እንተርናሽናል ሆቴል 300ሺህ ብር ሲቀጣ በጉለሌ ክ/ከተማ አቶ ሙሉጌታ መንጋ እና አቶ ናትናኤል ገበያው ድርጅት 300 ሺህ ብር ተቀጥተዋል።
ባለስልጣኑ ከዚህ በፊት ለህብረተሰቡ ሰፊ ግንዛቤ መስጠቱን ጠቁሟል።
ይሁን እንጂ ግለሰቦቹ እና ድርጅቶቹ ደንብ ተላልፈዉ በመገኘታቸዉ በድምሩ 2 ሚሊዮን 592 ሺህ ብር ተቀጥተዋል።
ባለስልጣኑ የአካባቢ ብክለት መከላከል እንዲቻል መረጃ በመስጠት የጠቆሙትን የህብረተሰብ ክፍሎች እያመሰገነ በቀጣይ ህብረተሰቡና ተቋማት ከዚህ ዓይነት ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስቧል።