የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል በይፋ ስራውን ጀመረ

You are currently viewing የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል በይፋ ስራውን ጀመረ

AMN – ጥቅምት 06/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የሚዲያ ልህቀት ማዕከል በይፋ ስራውን ጀምሯል።

በማዕከሉ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ መንግስት ሚዲያውን የሚያሻሽሉና ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የሪፎርም ስራዎችን እንደሰራ በመግለፅ፤ የሚዲያ ልህቀት ማዕከሉ ስራ መጀመር የሚዲያ ዘርፉን በማዘመንና በማሰልጠን የሀገርን ጥቅም ለማስከበር የሚሰሩ የሚዲያ ተቋማትን ለመፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚዲያዎችን በየትኛውም ሁኔታ እንደሚደግፍ የተናገሩት አፈ ጉባኤው፤ ሚዲያዎች ብሄራዊ ጥቅም ላይ ትኩረት ያደረጉ ዘገባዎችን ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማይረሱ፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ፣ ወደ አንድነትና ወደመሰባሰብ የሚያመጣ ትርክት የሚያራምዱና ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ የሚሰሩ መሆን አለባቸው ያሉት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮነን (ዶ/ር)፤ ማዕከሉ ኢትዮጵያን የሚመስል ሚዲያና ጋዜጠኞችን መፍጠር ግዴታ በመሆኑ ሙያተኞች በተለያዮ የጋዜጠኝነት ዘርፎች ስፔሻላይዝድ እንዲያደርጉ በማድረግ በቂ፣ የተጣራና ሚዛናዊ መረጃ ለአድማጭ ተመልካች ማድረስ እንዲችሉ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።

የሚዲያ ልህቀት ማዕከሉ በቴክኖሎጂ በታገዘ፣ በአንጋፋና ልምድ ባላቸው ሙሁራን ለጋዜጠኞች ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህም የኢትዮጵያን የጋዜጠኝነት ሙያ እንደሚያዘምነው ነው ሳምሶን መኮነን (ዶ/ር) የገለፁት።

የሚዲያ ልህቀት ማዕከሉ የታለመለትን አላማ ያሳካ ዘንድ፤ ከዚያም አልፎ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከተለያዮ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እና ተቋማት ጋር የአጋርነት ስራዎች እንደሚሰራ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ማዕከሉ በተለያዩ የጋዜጠኝነት ዘርፎች ስልጠና እንደሚሰጥ ሳምሶን መኮነን (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ ግልፅ ሀሳብን የያዙና የሚያራምዱ ብቁ ተቋማት ለመፍጠር ያስችል ዘንድ ከማዕከሉ ጋር በአጋርነት በመስራት ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ የአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በዋናነት ማዕከሉ ጋዜጠኞች ሀገራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ስራዎችን እንዲሰሩ፣ የሚዲያ ሙያ እንዲከበር፣ የጋዜጠኞች በነፃነት ሀሳብን የመግለፅ መብት እንዲከበር፣ ግሉልና ሙያውን የሚያከብሩ ሚዲያዎች እንዲፈጠሩና ሙያዊ ስነ-ምግባርን ያከበሩ የሚዲያ ተቋማት እንዲበረክቱ የሚሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ማዕከሉ የኢትዮጵያን ጋዜጠኝነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስና ተወዳዳሪ የሚያደርግ፤ እንዲሁም የሀገርን ጥቅም የሚያስከብሩ ሚዲያዎች የሚያበዛ መሆኑ ታምኖበታል፡፡

የሚዲያ ልህቀት ማዕከሉ በይፋ ስራውን በጀመረበት መድረክ የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review