የሰው ልጅ እድሜ ጠገብ የግንባታ መሳሪያ የሆነው እንጨት (ጣውላ) ከብረት በጥንካሬ ልቆ መመረቱ ተሰምቷል።
በአሜሪካ የሚገኝ ኩባንያ ከአመታት ምርምር በኃላ ከብረት አስር እጥፍ የሚበልጥ ጥንካሬ ያለው እንጨት ማምረት መጀመሩን ይፋ አድርጓል። “ሱፐር ውድ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የእንጨት አይነት ከብረት በጥንካሬ ከመብለጡ ባሻጋር በ6 እጥፍ ክብደት እንደሚያንስ ሲኤንኤን አስነብቧል።
የምርምሩ ባለቤት የሆኑት የሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ሊያንግቢንግ ሁ አሁንም ድረስ ተመራጭ የግንባታ ግብአት የሆነውን እንጨት በተሻለ ደረጃ ለማሻሻል ምርምር የጀመሩት ከአመታት በፊት ነበር። ፕሮፌሰሩ የእጽዋት ፋይበር ዋና አካል የሆነውን “ሴሉሎስን” በመጠቀም እና ከሌሎች ኬሚካሎች ጋር በማዋሀድ የእንጨትን ጥንካሬ ማሳደግ መቻላቸውን ተናግረዋል።
እንጨቱ በቅድሚያ በውሀ እና በተመረጡ ኬሚካሎች ውህድ የሚቀቀል ሲሆን ቀጥሎም ሌሎች ሂደቶችን በማለፍ በሚፈለገው የጥንካሬ ደረጃ ላይ ደርሷል። በአሁኑ ወቅት ከ140 በላይ የፈጠራ ባለቤትነት ማረጋገጫዎች በማቅረብ ለገበያ የቀረበው “ሱፐር ውድ” የግንባታዎች አጠቃላይ መዋቅር ቀለል ብሎ እንዲሰራ የሚያስችል ነው ተብሏል።
በተጨማሪም የመሬት መንቀጥቀጥን ለመቋቋም ፣ የግንባታዎችን መሰረት በቀላሉ ለመገንባት እንዲሁም ግንባታን ቀላል እና ፈጣን ለማድረግ ተመራጭ እንደሚሆን ተመራማሪው ተናግረዋል።
“ኢንቨንት ውድ” የተሰኘው በአሁኑ ወቅት ፈጠራውን በማምረት ለንግድ እያቀረበ የሚገኘው ተቋም እንጨቱን ከግንባታ ግብአትነት ባለፈ ለቤት እና ለቢሮ መገለገያ ቁሳቁሶች (ፈርኒቸር) መስሪያነት በሰፊው እንደሚውል ገልጿል።
በዳዊት በሪሁን