የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በ2025 የIMF እና ዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባዎች ላይ ለመሳተፍ ከተገኙ ዓለማቀፍ ከፍተኛ ባለሀብቶች ጋር ጎን ለጎን በዋሽንግተን ዲሲ በመገናኘት ተወያይተዋል።
ስታንዳርድ ባንክ ግሩፕ የተሰኘ ተቋም ባዘጋጀዉ በዚህ መድረክ ላይ ከአለም አቀፍ ተቋማት ባለሀብቶች ጋር በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ የሪፎርም ስራዎች፣ የዕድገት ሁኔታ እና እምቅ የኢንቨስትመንት እድሎች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይቶችን አካሂደዋል።

የባለሃብቶች የውይይት መድረኩ ከአውሮፓ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከአፍሪካ የተውጣጡ ታዋቂ ባለሀብቶችን ያካተተ ነዉ። ውይይቱ በአፍሪካ ኢኮኖሚ እና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ሀሳብ እንዲለዋወጡ ያስቻለ መድረክ መሆኑ ተገልጿል።
ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን በመወከል ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ልዩ መድረክ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ የሪፎርም ስራዎች፣ የዕድገት ሁኔታ እና እምቅ የኢንቨስትመንት እድሎች በዳሰሰ መልኩ ሰፊ ማብራሪያዎችን ለታዳሚዎች አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በዘንድሮው የIMF እና የአለም ባንክ አመታዊ ስብሰባዎች መድረክ ላይ የኢትዮጵያን አለም አቀፍ አጋርነቶችን ለማጠናከር፣ የፖሊሲ ግልፅነትን ለመፍጠር እንዲሁም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ተወዳዳሪና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት በሚገባ ያስገነዘበበት መድረክ እንዲሆን አድርጓል።
በወንድማገኝ አሰፋ