በንግድ ልማት ጉባኤውና አውደ ርዕዩ ላይ ከ150 በላይ የፓኪስታን አምራች ድርጅቶች እየተሳተፉ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በመክፈቻው መርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ በር መሆኗን ጠቅሰው፣ በሀገሪቱ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ምህዳር መኖሩን አስገንዝበዋል።
መንግሥት ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም፣ በኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን በማንሳት፣ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪና ሌሎችም ዘርፎች ሰፊ አቅም እንዳለ ነው የጠቀሱት።
ኢትዮጵያን ጠንካራ የንግድ ማዕከል ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንና የኢኮኖሚ ልማት ዕድገቷን የሚያስቀጥሉ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እየገነባች መሆኗን ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የግብርና ስራዎች፣ የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነት፣ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክቶች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ፓኪስታንን ጨምሮ ከሌሎች የዓለም ሀገራት በርካታ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ በበኩላቸው፣ የንግድ ልማት ጉባኤው በፓኪስታን እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ አጋርነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
በጉባኤውና በተዘጋጀው አውደ ርዕይ ከ150 በላይ የፓኪስታን ኩባንያዎች መሣተፋቸውን ጠቅሰው፣ ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአውደ ርዕዩ የሕክምና መድኃኒት ምርትና መሣሪያዎች፣ የውበትና የቆዳ እንክብካቤ ውጤቶች፣ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች፣ የምግብና የምግብ ነክ የግብርና ምርቶች፣ የአውቶሞቲቭ መለዋወጫና ሌሎችም ምርቶች ቀርበዋል።