የዓለም ጤና ድርጅት በጃፓን መንግስት ትብብር በትግራይ ክልል ለሚገኙ ሶስት ሆስፒታሎች የመልሶ ግንባታና የአምቡላንስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የዓለም ጤና ድርጅትና የጃፓን መንግስት በጤና ዘርፎች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀው፤ ድርጅቱ ከመንግስትና አጋር አካላት ጋር በመሆን የጤና ስርዓቱን ለማጎልበት ላበረከተው አስተዋፅኦ አመስግነዋል። ኢትዮጵያና ጃፓን ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን አንስተው፤ ጃፓን በጤናው ዘርፍ ያላት አበርክቶ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለሰው ሰራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት ከአጋር አካላት ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ እንደምታጠናክርም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ቺሳካ እንዳሉት፤ የጤናው ዘርፍ ላይ መሰረት ያደረጉ የትብብር ተግባራት የጤና ስርዓቱን ለመገንባት ያግዛሉ።
በጃፓን ኤምባሲ የሚሲዮኑ ሁለተኛ ተጠሪ ኔት ሱ ሸንታሮ በበኩላቸው፤ ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ዘርፈ ብዙ ትብብር እንዳላት አመልክተው፤ ትምህርት፣ ጤናና ግብርና በትብብር ከሚሰራባቸው መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።
የሀገራቱን ትብብር የበለጠ ለማስፋትና ለማጠናከር እንደሚሰሩም ተናግረዋል። በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አማኑኤል ሀይለ በበኩላቸው፤ በክልሉ ያሉ ሶስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የእናቶችና ህፃናት ህክምና መስጠት የሚያስችል መልሶ ግንባታ እንደተከናወነላቸው አስታውቀዋል።