ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ የከተማችንን ታማኝ ግብር ከፋዮች በታላቅ ድምቀት ሸልመናል ፤ ተሸላሚ ግብር ከፋዮቻችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ዉድ ታማኝ ግብር ከፋዮች መዲናችን ከእናንተ በምትሰበስበዉ ገቢ በከተማችን በአስደናቂ ሁኔታ የተገበርናቸዉ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማት ፣ የህዝቡን የኑሮ ጫና ያቀለሉ ስራዎች ፣ የተማሪዎች ምገባ፣ ከተማችንን ለቢዝነስ እና ለመኖር የተመቸች ንፁህ ፣ ጤናማ አካባቢ እና በአለም አቀፍ ደረጃም ተመራጭና ተወዳዳሪ እየሆነች ይገኛል ፤ ይህ ለዉጥ በርግጥ ለእናንተም ተጨማሪ አሴት፣ለቢዝነስ ማህበረሰቡ ተጨማሪ የሀብት መፍጠሪያ ምንጭ ነዉም ብለዋል፡፡
በቀጣይ በግብር አሰባሰብ ዙሪያ የአገልግሎት አሰጣጣችንን ይበልጡን ዲጂታላይዝ በማድረግ ፣ በማዘመን እና ተጠያቂነትን በማስፈን ክፍተቶችን እየሞላን ፣ እፀፆችን እያረምን የሁለንተናዊ ብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ከተማን እየገነባን እንሄዳለን በማለት ገልፀዋል።
በዛሬዉ የእዉቅና እና የሽልማት መርሃ ግብር ለእዉቅና የበቃችሁ ግብር ከፋዮቻችን ለታማኝነታችሁ ምስጋናዬ የላቀ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በተለይም የወርቅ እና የፕላቲኒየም ደረጃ ግብር ከፋዮች የዘርፉ አምባሳደሮቻችን በመሆናችሁ በከተማችን በየትኛዉም መንግስታዊ አገልግሎት እና ኩነት የቅድሚያ ቅድሚ እንድትስተናገዱ እና VIP ፕሮቶኮል እንዲሰጣችሁ መወሰናችንን ስገልፅ ሌሎችም የእናንተን አርአያነት እንደሚከተሉ በማመን ነዉ ብለዋል፡፡