ትውልዱ የሀሰት ትርክቶችን በመመከት የራሱን አሻራ ማኖር ይጠበቅበታል

You are currently viewing ትውልዱ የሀሰት ትርክቶችን በመመከት የራሱን አሻራ ማኖር ይጠበቅበታል

AMN – ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም

‎የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአንድነታቸዉ እና የወንድማማችነታቸዉ ማህተም የሆነዉን ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በአንድነት ገንብተዉ በህብረት አስመርቀዋል፡፡

የዉስጥና የዉጪ ጫናን ጨምሮ በርካታ ዉጣ ዉረዶችን በማለፍ፤ የላብ፤ የእንባ፤ የዉሃና የደም እንባ በመክፈል በጉባ ሰማይ ስር የወል ታሪካቸዉን በደማቅ ቀለም ጽፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ከድህነት እንዳትላቀቅና የብልጽግና ጉዞዋን እንዳታረጋግጥ ከፍተኛ ማነቆዎችን ከፈጠሩበት አበይት ምክንያቶች አንዱ በተለይ በግብጽ መንግስት በኩል ለዘመናት ሲደርስባት የነበረዉ ዘርፈ ብዙ ጫና መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

‎የግብጽ መንግስት የኢትዮጵያን የመልማትና የማደግ ፍላጎት ከመግታትና ከማደናቀፍ ባሻገር በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን በተለያዩ መንገዶች ተጽእኖና ጫና ሲፈጥር እንደነበረና አሁንም የተለያዩ ጫናዎች ለማሳደር በመታተር ላይ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይጠቁማሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ጥናት እና የምርምር ተቋም መምህር መሀመድ ሀሰን (ዶ/ር ) የግብፅ መንግስት የሚያቀርበው ማንኛውም ክስ የኢትዮጵያን የመልማት እርምጃ ለመግታት እና በአጠቃላይ ሀገሪቱን ለማፍረስ የቆየ ታሪካዊ ጠላትነትን ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የግብጽ በመንግስት በፖለቲካ፤ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች በኢትዮጵያ ላይ ከሚያደርሰው ጫና ባሻገር በነፃ አውጪ ድርጅቶች ስም ታጣቂዎችን በማሰልጠን ጭምር ህዝቡን በተለያዩ አጀንዳዎች ስታጋጭ እንደኖረች መሀመድ ሀሰን (ዶ/ር) ያብራራሉ።

‎የግብፅ መንግስት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት ሃገሪቱ ደካማ መንግስት እንዲኖራትና እራሷ ችላ እንዳትቆም የማድረግ ሴራ፣ ምኞት እና የዘመናት ፍላጎት እንደነበራትም አስረድተዋል።

‎ታጣቂዎችን በማስታጠቅ ብቻ ያላበቃው የግብፅ ሴራ ፣ በኢትዮ – ሶማሊያ ጦርነትን ጊዜ ሶማሊያን በማስታጠቅ መተባበሯን ወደ ኋላ ሄደው ታሪክን አስረጂ ያደርጋሉ ።

‎ግብፅ ኢትዮጵያን የማዳከም እና የማደህየት ፍላጎት እንዳላትም ነው መምህሩ ያስረዱት ። ግብጽ ” ኢትዮጵያ ደካማ እና ደሀ ሃገር ከሆነች እኔ ፍላጎቴን ማሟላት እችላለሁ” ብላ እንደምታምን ነው መሀመድ ሀሰን (ዶ/ር) የገለፁት ።

‎ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ መገንባቷ ለጋራ ልማት ያላትን ፅኑ ፍላጎት እና የፍትሀዊነት መርህ ማሳያ ነው ያሉት መሀመድ (ዶ/ር) ፣ ይህ እሳቤ የኢትዮጰያ ፍትሀዊ አቋም አለም አቀፍ ተቀባይነትን እያገኘ መምጣቱን ተናግረዋል ።

‎ኢትዮጵያ በጋራ የማደግ ፍላጎት እንዳላት ግብፅን ጨምሮ የአለም ህዝብ የሚያውቀው እውነታ ነዉ ያሉት መሀመድ (ዶ/ር) ፣ በአሁን ጊዜ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ አለም ወደ ኢትዮጰያ ያዘነበለው እውነታውን በመገንዘቡ ነው ብለዋል ።

‎አለም በጋራ ሰርቶ የመልማት ባህልን እያዳበረ ባለበት ዘመን ግብፅ እያራመደች ያለችው እሳቤ ስሁት ትርክትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ፣ ይህም ወንዝ የማያሻግር እና ውሀ የማያነሳ እርምጃ ነው ብለውታል ።

‎ግብፅ ከኢትዮጰያ ጋር አብሮ የመስራት እና የመልማት ምርጫ ብቻ እንዳላት ገልፀው ፣ ከአሁን ቀደም ስትከተለዉ የነበረዉ ስትራቴጂ ግዜውን የማይዋጅ ሴራ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

‎ኢትዮጵያ በተለያዩ ግዜአት የገጠሟትን ፈተናዎች በብርቱ ልጆቿ ክንድ መክታ ዛሬ ላይ ደርሳለች ያሉት (ዶ/ር) አሁንም ያሉባትን ተፅዕኖዎች ትውልዱ ሊመክተዉ ይገባል ብለዋል::

‎የኢትዮጵያ ከፍ ማለት እና መለወጥ የሚጠቅመው ትውልዱን መሆኑን አስረድተዋል ። ይህ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይገባዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review