ሚካኤል አርቴታ አምስት ዓመት ተጫውቶ ያሳለፈበትን ክለብ ለማሰልጠን ሲመጣ ነገሮች ቀላል አልነበሩም፡፡ የማይተካ ሚና የነበራቸው የሚመስሉት አርሰን ቬንገር ከለቀቁ በኋላ ክለቡ አቅጣጫው ወዴት እንደሆነ ለመተንበይ ያስቸግር ነበር፡፡
በሰሜን ለንደኑ ክለብ 22 ዓመት የቆዩት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ በኡናይ ኤምሬ ተተኩ፡፡ ስፔናዊው አሰልጣኝ የሁለት ዓመት ውል ቢፈርሙም ውላቸውን ሳይጨርሱ ተሰናበቱ፡፡ በመጀመሪያ የውድድር ዓመታቸው የዩሮፓ ሊግ ፍፃሜ መድረስ የቻሉት ኡናይ ኤምሬይ በቀጣዩ ዓመት ከህዳር ወር አላለፉም፡፡
ክለቡ በጊዜያዊነት ታሪካዊ ተጫዋቹ ፍሬዲ ዩንበርግ ከያዘው በኋላ ከፔፕ ጋርዲዮላ ጋር የሰራው የቀድሞ ልጁ ሚካኤል አርቴታን በቋሚነት ሾመ፡፡ በዋና አሰልጣኝነት የመጀመሪያ ክለቡ የሆነው አርሰናልን ቅርፅ ለማስያዝ ብዙ የለፋው አርቴታ አሁን ፍሬውን እየተመለከተ ይገኛል፡፡
በእርግጥ ለዝውውር ካወጣው ወጪ አንፃር ዋንጫ አለማንሳቱን እንደክፍተት የሚያነሱ አሉ፡፡ አርቴታም ወቀሳውን ቢቀበልም ቡድኑን በወጥነት እንዲፎካከር ግን አድርጎታል፡፡ ባለፈው ዓመት ለሦስተኛ ተከታታይ የውድድር ዓመት 2ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው አርሰናል ዘንድሮ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ጠንክሮ የመጣ ይመስላል፡፡

መድፈኞቹ ዘንድሮ በሁሉም ውድድር 10 ጨዋታ አድርገው አንድ ብቻ ተሸንፈዋል፡፡ በፕሪምየር ሊጉ በአንፊልድ በሊቨርፑል 1ለ0 የተረቱበት ውጤት ብቸኛ እጅ የሰጡበት ጨዋታ ነው፡፡
ከሊቨርፑሉ ጨዋታ ውጪ የመድፈኞቹ ጉዞ ተስፋ ሰጪ ይመስላል፡፡ አሁን ላይ ደጋፊዎች ይህ ዓመት የእነርሱ ሊሆን እንደሚችል እያመኑ መጥተዋል፡፡ አርሰናል ከሰባት የሊግ ጨዋታ ከማንችስተር ዩናይትድ ፣ ሊቨርፑል እና ኒውካስትል ዩናይትድ ጋር ከሜዳቸው ውጪ ለመጫወት ተገዷል፡፡ ማንችስተር ሲቲን ደግሞ በሜዳቸው ኤምሬትስ አስተናግደዋል፡፡ እነዚህን ፈታኝ ጨዋታዎች ለማድረግ ቢገደዱም የሊጉ መሪ ከመሆን አላገዳቸውም፡፡
የተከላካይ ክፍላቸው ጥንካሬውን አስቀጥሏል። በሊጉ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች የተቆጠረባቸው ሦስት ግብ ብቻ ነው። ይህም የፕሪምየር ሊጉ ቀዳሚው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው አስብሏቸዋል። መድፈኞቹ ያስቆጠሯቸው 14 የሊግ ግቦች የሚበለጠው 15 ግብ ማስመዝገብ በቻለው ማንችስተር ሲቲ ብቻ ነው።
የማጥቃት ሃይላቸው ከሌሎችም ሎቆ እንዲታይ ያደረጉ በርካታ ቁጥራዊ ማሳያዎችም አሉ። የአርሰናል ተጫዋቾች በሊጉ በተጋጣሚያቸው የግብ ክልል 249 ጊዜ ኳስ ነክተዋል። በዚህ መለኪያ ከተከታያቸው በ43 ይበልጣሉ። በበርካታ አጋጣሚ አርሰናል የቆሙ ኳሶች ጥገኛ እንደሆነ ቢነገርም የማጥቃት አማራጮች እንዳሉት እያሳየ ይገኛል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት የፈረሙ ተጫዋቾች ፍሬያቸው እየታየ ነው። ማርቲን ዙብሜንዲ ለመላመድ ጊዜ አላስፈለገውም። ጉዳት የገታው ኖኒ ማድኤኬ ጅማሮው ከአይን ያውጣህ የሚያስብል ነበር። ኤቤሬቺ ኤዜ የበለጠ ምቾት እየተሰማው መጥቷል። እንደተጠበቀው ግብ ባያስቆጥርም ቪክቶር ዮኬሬሽ ለቡድኑ ሌላ አማራጭ እየሰጠ ይገኛል።
ስዊድናዊው አጥቂ ያለኳስ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል 49 ጊዜ ሩጫዎችን በማድረግ ታታሪነቱን አሳይቷል። ለጊዜው ነገሮች የሰመሩለት የሚመስለው አርሰናል የሚያሳስበው የአምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድ ጉዳት ብቻ ነው። አርሰናል የሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ ከፈለገ ምንም ድርድር የሌለው በየሳምንቱ ወጥነቱን ጠብቆ ማቆየት ይኖርበታል።
ሊቨርፑል በአርነስሎት እየተመራ ከ10 ኛው ሳምንት በኋላ የሊግ ቀዳሚነቱን ለማንም ሳያስነካ ዋንጫውን ከፍ አድርጓል። አርሰናል በመጨረሻም ከ21 ዓመት በኋላ የሊጉን ዋንጫ የሚያነሳበት ጊዜ ዘንድሮ ይሆን? ቀጣዮቹ ስምንት ወራት መልሱን ይሰጡናል።
በሸዋንግዛው ግርማ