የባከነ ተሰጥዖ ወይስ ?

You are currently viewing የባከነ ተሰጥዖ ወይስ ?

AMN-ጥቅምት 06/2018 ዓ.ም

የብራዚል ምድር ስሙን በእግር ኳስ ታሪክ ህያው የሚያደርግ ሌላ ባለተሰጥኦ እንዳፈራ ተነገረ። በተለይ በባርሰሎና ቆይታው ከቡድን አጋሮቹ ሊዮኔል ሜሲ እና ሊውስ ስዋሬዝ ጋር የፈጠረው ጥምረት ድንቅ ብቻ ተብሎ የሚታለፍ አልነበረም።

ኔይማር ጁኒየር ዳ ሲልቫ የባሎን ድኦሩን ዙፋን እንደሚቆጣጠር በድፍረት መናገር ያስችል ነበር። ነገሮች ግን በታሰቡት ልክ አልሆኑም። ስፔንን ለቆ ወደ ፈረንሳይ ካቀና በኋላ ብዙዎችን ያሳመነ ከፍታ ላይ አልደረሰም። ለምን? ተከታዩ ፅሁፋችን ይዳስሰዋል፡፡

እንግሊዛዊው የስፖርት ጋዜጠኛ ማይክል ኮክስ ኔይማር ጁኒየር ከምንግዜውም ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋቾች መሀል መመደብ አለበት ይላል። ’’The athletic ’’ ላይ ባሰፈረው ፅሁፉ ያስቀመጣቸው መከራከሪያዎች አሉ።

በበርካቶች ዘንድ ታላቅነታቸው የተመሰከረላቸው ብራዚላውያንን በመጥቀስ በወጥነት ብቃትን ጠብቆ መዝለቅን ግዴታ ባደረገው የአውሮፓ የክለብ እግር ኳስ ውስጥ እንደ ኔይማር ተፅእኖ ፈጣሪ እንዳልነበሩ በማሳያነት ያነሳል።

ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ ፣ ሪቫልዶ ፣ ሮናልዲንሆ እና ካካ ስማቸው የገዘፈ ቢሆንም የኔይማርን ያህል ወጥነት እንዳልነበራቸው ማሳያዎችን በማቅረብ የስፖርት ቤተሰቡን ለሙግት ይጋብዛል።

ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ በ14 አመት የአውሮፓ ቆይታ አንድ የሊግ ዋንጫ ብቻ አንስቷል። በቻምፒየንስ ሊግ ደግሞ ለፍፃሜም ደርሶ አያውቅም።

ሪቫልዶ በአውሮፓ አምስት አመት ብቻ ነው የቆየው።በባርሰሎና አስደናቂ አምስት አመታትን ቢያሳልፍም ሮናልዲንሆ ገና በ28 አመቱ ጫማ ለመስቀል የተቃረበ ይመስል ነበር።

ካካ በኤሲሚላን ኮከብ ሆኖ በሪያል ማድሪድ ከስሟል። ከእነዚህ ኮከብ ብራዚላውያን አንፃር ኔይማር በወጥነት መጫወት ችሏል። ስለዚህ ተሰጥኦውን እንዳባከነ መቆጠር የለበትም ይላል ማይክል ኮክስ።

የኔይማር ተሰጥኦ ላይ ክርክር የሚያነሳ ማግኘት ይከብዳል። ፀጋውን የበለጠ አሳድጎ ካሳካውም በላይ ታላላቅ ድሎችን ማግኘት እንደነበረበት የሚሞግቱ ግን የትየለሌ ናቸው። የኔይማር የባርሴሎና ቆይታ ስኬታማ ተብሎ ሊነገርለት ይችላል።

አንድ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች የሚመኛቸውን ዋንጫዎችን አሳክቷል። ከሊዮኔል ሜሲ እና ሊውስ ስዋሬዝ ጋር የፈጠረው ጥምረት ድንቅነት ቢተነተን አንድ መፅሐፍ ይወጣዋል።

የአራት አመት የካታላን ቆይታው በስምንት ዋና ዋና ዋንጫዎች ታጅቦ ተጠናቋል። ትልቁ ክርክር የሚመጣው ወደ ፓሪሰን ዠርማ አቅንቶ በፈጠረው ተፅዕኖ እና ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን በሰጠው ግልጋሎት ላይ ነው።

እ ኤ አ በ2017 የውል ማፍረሻው ተከፍሎለት ፓሪስ የደረሰው ኔይማር የክለቡ ምልክት ተደርጎ ተቆጠረ። አሁንም ድረስ የትኛውም ክለብ ደፍሮ ያላሻሻለው 222 ሚሊየን ዮሮ ተከፍሎበት የመጣው ኮከብ በገዛ ደጋፊዎቹ ተጮሆበታል። የስታዲየም አልበቃ ብሏቸው ወደ መኖሪያ ቤቱ በማቅናት የተቃውሞ በትራቸውን ሰንዝረውበታል።

የክለቡን ምስል እንዲቀይርላቸው ያመጡት የፓሪሰን ዠርማ ባሌቤት ናስር አል ኸልኸይፊ ሁሌም ድጋፋቸውን ቢያሳዩትም ደጋፊዎች ጉዳያቸው አልሆነም። ተደጋጋሚ ጉዳቱ ተስፋ ያስቆረጣቸው ደጋፊዎች ከወጣበት ገንዘብ አንፃር ያበረከተው ወይንም የሰጠን ጥቂት ነው ባዮች ናቸው።

ኔይማር በፒ ኤስ ጂ ማድረግ ከሚጠበቅበት የጨዋታ ብዛት 55 በመቶ ብቻ ነው የተጫወተው። በሰባት አመት ቆይታው በሁለት የውድድር አመት ላይ ብቻ ነው 30 እና ከዚያ በላይ ጨዋታዎችን ማከናወን የቻለው።

የፓሪሰን ዠርማ ደጋፊዎች በኔይማር ቆይታ ያገኙትን አምስት የሊግ ዋንጫ ከቁብ አልቆጠሩትም። ሦስት ኩፕደ ፍራንስ እና ሁለት ኩፕደ ላ ሊግ ዋንጫዎች ምናቸውም አይደለም።

የፈለጉት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግን ነበር። በ2019/20 የውድድር ዓመት በቶማስ ቱኸል እየተመሩ ለፍፃሜ ደርሰው በባየርን ሙኒክ ተሸንፈው ዋንጫውን አጥተዋል። ኔይማር በሽንፈቱ አዝኖ እንባውን ቢያፈስም የራራለት ደጋፊ ብዙ አልነበረም።

ከሊዮኔል ሜሲ ጥላ ወጥቶ የራሱን ዝና ለማግዘፍ ፓሪስ ያቀናው ኔይማር የደጋፊዎች ትችት አንገሽግሾት ወደ ባርሰሎና ለመመለስ የጣረበት ጊዜ በርካታ ነበር።

ጉዳት ሰቅዞ በየዘው የሰባት አመት የፈረንሳይ ቆይታው 173 ጨዋታ አከናውኖ በ195 ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል። 118ቱን በማስቆጠር 77 ቱን ለቡድን አጋሮቹ በማቀበል።

በጥቂት ሙገሳ በበርካታ ተቃውሞ ታጅቦ የክለብ እግር ኳስ ህይወቱን በሳውዲ አረቢያ ለአል ሂላል በመፈረም ቢቀጥልም ብዙ አልቆየም፡፡ የልጅነት ክለቡ ሳንቶስን ቢቀላቀልም ጉዳት ያሰበውን እንዲያሳካ እድል አልሰጠውም፡፡

ኔይማር ለሀገሩ ብራዚል በሰጠው አገልግሎትም ከትችት አልዳነም፡፡ 79 ግቦችን አስቆጥሮ የብሔራዊ ቡድኑ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቢሆንም ዋንጫ አለማሸነፉ እንደ ጉድለት ይነሳበታል፡፡

እናንተስ ኔይማር ጁኒየርን ከታላላቅ ተጨዋቾች መደብ በየትኛው ደረጃ ቢቀመጥ ይመጥነዋል ትላላችሁ ? መልሱን ለእናንተ ትተናል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review