በየአመቱ ጥቅምት 6 የአለም የምግብ ቀን በሚል ተሰይሞ ላለፉት 80 አመታት ተከብሯል።
ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቃት በኃላ በተመሰረተው የአለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ባለቤትነት የሚከበረው በዓል የምግብ ዋስትና የተረጋገጠበት ነገን እውን ለማድረግ ከማሰብ የመነጨ ነው።
የምግብ አቅርቦት እና ፍጆታ በእጅጉን የተሳሰረ እንደሆነ ይነገራል፤ ሆኖም በአንደኛው የአለም ክፍል ሚሊየኖች በምግብ እጥረት ሲቸገሩ በሌላው አካባቢ ደግሞ ከመጠን ባለፈ ውፍረት የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም።
በአሁኑ ወቅት ከአለም አቀፍ አጠቃላይ ምርት አንድ ሶስተኛው ወይም 1.3 ቢሊየን ቶን ምግብ በየአመቱ እንደሚባክን የወርልድ ፖፕሌሽን ሪቪው መረጃ ይጠቁማል።
የምግብ ብክነት የሚከሰተው ከምርት እና ከስብሰባ ሂደቱ ጀምሮ በመኖሪያ ቤት ወይም ምግብ በሚሸጥባቸው አካባቢዎች ባለ የመጠን እንዲሁም የአጠቃቀም ችግር አንደሆነ መረጃው ይጠቁማል።
የአለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ፋኦ ባወጣው መረጃ በአለም አቀፍ ደረጃ 673 ሚሊየን ሰዎች ረሃብ ውስጥ ይኖራሉ ብሏል። ይህ የሚባክነው ምግብ በተለያዩ የአለም ክፍሎች በረሃብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በበቂ መመገብ የሚችል ነው፡፡
በገንዘብ ሲተመን ወደ አንድ ትሪሊን ዶላር እንደሚጠጋ ለሚገመተው ብክነት በመኖርያ ቤቶች የሚባክነው ምግብ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ መኖርያ ቤቶች 61 በመቶ የብክነት ድርሻ ሲኖራቸው፣ የምግብ መሸጫዎች (ሆቴል እና ሬስቶራንቶች) ደግሞ 26 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡
በቢሊየን የሚቆጠር ህዝብ ያላቸው ቻይና እና ህንድ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ምግብ አባካኞች ተብለው በደረጃ ተቀምጠዋል። በባለፈው አመት 91 ሚሊየን ቶን ምግብ ስታባክን የነበረችው ቻይና፤ በዚህኛው አመት ከ108 ሚሊየን ቶን በላይ በማባከን አንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ህንድ 78 ሚሊየን ቶን በማባከን ሁለተኛ ስትሆን ፓኪስታን 30 ሚሊየን እንዲሁም ናይጄሪያ በ24 ሚሊየን ቶን ትከተላላች። ምግብ በከፍተኛ ደረጃ የሚያባክኑ 10 የአለም ሀገራት ደረጃን ከስር ካለው መረጃ ይመልከቱ።
በዳዊት በሪሁን