ኢትዮጵያ እና ቻይና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን በሚያረጋግጡ መስኮች አጋርነታቸውን ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

You are currently viewing ኢትዮጵያ እና ቻይና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን በሚያረጋግጡ መስኮች አጋርነታቸውን ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

AMN ጥቅምት 7/2018

ኢትዮጵያ እና ቻይና የጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በሚያስጠብቁ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እና ለማስፋት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ይገኛል።

በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዓመታዊ ስብስባው ላይ እየተሳተፈ ነው።

ልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካተተ ነው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከስብስባው ጎን ለጎን ከቻይና ህዝባዊ ባንክ የሚል ስያሜ ካለው የአገሪቱ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ፓን ጎንግሼንግ ጋር ምክክር አድርገዋል።

ውይይቱ የኢትዮጵያ እና ቻይና የፋይናን እና ኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከርን ያለመ ነው።

ድንበር ተሻጋሪ ንግድን ማሳለጥ፣ በሀገር ውስጥ የመገበያያ ገንዘብ ክፍያዎችን መፈጸም እና የእዳ ሽግሽግ በውይይቱ ከተነሱ ሀሳቦች መካከል ይጠቀሳሉ።

የሁለቱ ብሄራዊ ባንኮችን ትብብር እና የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰት ከሚደግፉ አጋዥ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስርን ማጠናከር በሚቻልባቸውን እድሎች ላይም ምክክር ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በክፍያ ስርዓቶች፣ የሀገር ውስጥ ምንዛሪ ልውውጦች እና የፋይናንስ ዘርፍን ጨምሮ ስትራቴጂካዊ አጋርነቷን ማጠናከር እንደምትሻ አመልክተዋል።

የትብብር መስኮቹ ከኢትዮጵያ ሀገር በቀል የሪፎርም አጀንዳዎች ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ሁለቱ ወገኖች ቴክኒካል ውይይቶችን ለመቀጠል እና የሀገራቱን ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥቅሞች በሚያረጋግጡ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የገንዘብ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ተዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review