የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮግራም (RUFIP III) ሶስተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ የሚውል የ110 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ይገኛል።
በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዓመታዊ ስብሰባው ላይ እየተሳተፈ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከአውሮፓ ኮሚሽን እና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።
አቶ አሕመድ ከአውሮፓ ኮሚሽን የዓለም አቀፍ አጋርነት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ማርጄታ ጃገር ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ስትራቴጂካዊ የሆኑ ቀጣናዊ የመሰረተ ልማት ኮሪደሮች ላይ ያለውን ትብብር ማጠናከር፣ የኢትዮጵያ የሪፎርም ፕሮግራሞች ድጋፍ ማድረግ እና ትብብሮች ከቁልፍ የመንግስት ትኩረቶች ጋር ማጣጣም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
በተጨማሪም የገንዘብ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ የኢንቨስትመንት ባንክ ከዓለም አቀፍ አጋርነት ዳይሬክተር ቱራያ ትሪኪ ጋር ውይይት አድርገዋል።
ሚኒስትሩ ባንኩ የኢትዮጵያ የልማት አጀንዳ በተለይም አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን፣በንጹሕ መጠጥ ውሃ እና በሕዝብ ጤና አጠባበቅ ላይ ላተኮሩት ፕሮጀክቶች (ዋሽ) እና የሴቶች የፈጠራ ልማት እያደረገ ያለውን የፋይናንስ ድጋፍ አድንቀዋል።
አቶ አሕመድ የኢንቨስትመንት ባንኩ የኢትዮጵያ ዋንኛ ትኩረቶችን መሰረት በማድረግ ድጋፍ ሊያደርግባቸው የሚችሉ መስኮችን አስመልክቶ ሀሳባቸውን አንስተዋል።
ሁሉን አቀፍ የገጠር እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት ኢኒሼቲቭ (RISED) እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለአብነት ጠቅሰዋል።
በውይይቱ ወቅት የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በገጠር አካባቢዎች ያሉ ዜጎች የፋይናንስ አቅርቦት ማሳደግን ፤የፋይናንስ አካታችነት ማረጋገጥንና የኢትዮጵያ አጠቃላይ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ጥረቶች መደገፍ አላማ ያደረገውን የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮግራም የሶስተኛ ምዕራፍ ትግበራ የ110 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል።
ውይይቶቹ የኢትዮጵያ መንግስት እና የአውሮፓ ህብረት ተቋማት በዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ልማት ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር፣የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ የገንዘብ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡