አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሀሰት ትርክቶችን ከማረምና ትክክለኛ ዘገባዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ረገድ ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃጸም ገምግሟል፡፡
በግምገማ መርሐ-ግብሩ አቶ ብዙዓለም ቤኛ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
በሪፖርታቸውም በይዘት ተደራሽነት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በዲጂታል ሚዲያ እና የገቢ እድገት እንዲሁም በሽያጭ አፈፃጸም የተመዘገቡ ስኬቶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በዚህም ይዘቶችን በሁሉም የሚዲያ አማራጮች በሚገባ መተግበር፣ ወቅታዊ የቀጥታ ስርጭቶችን ተደራሽ ማድረግ፤ የይዘት ጥራት መጨመር እና ተባባሪ አዘጋጆችን መሳብ መቻሉ ከጥንካሬዎች መካከል የጠቀሷቸው ናቸው፡፡
ሪፖርቱን ተከትሎ አስተያየት የሰጡ የቋሚ ኮሚቴው ዓባላትም፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሁሉም ዘርፍ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ መሀመድ ገልማ (ዶ/ር)፣ ተቋሙ በአደረጃጀቱ እና በውስጥ አሰራሩ የተሻለና ዘመናዊነትን የተላበሰ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚያቀርባቸውን የይዘት ሥራዎችም አዝናኝ እና አስተማሪ በመሆናቸው የሀሰት ትርክት ለሰለቸው ማህበረሰብ ትክክለኛ ተመራጭና የሁሉም ቤት እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡ የምክር ቤት አባላትም፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በከተማ አስተዳደሩ እውቅና እንደተቸረው በማስታወስ፣ ይህ እውቅናም ህዝብና መንግስትን በማገናኘት ረገድ ውጤታማ ሥራ በመስራቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በመዲናዋ ብሎም በሃገር አቀፍና አለም አቀድ ደረጃ ተመራጭና ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን አልፎ አልፎ የሚታዩ ውስንነቶችን በማስተካከል በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በዲጂታል ሚዲያ አማራጭ የያዘውን አቀራረብና የፈጠራ ሥራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸዉ ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች እና ውስንነቶች በሚገባ ማንሳቱን ጠቅሰው፣ ጠንካራ ጎኖቹን በማስቀጠል ውስንነቶችን ደግሞ ለመቅረፍ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በታምራት ቢሻው