የከተማዋ የዕድገት መሰላል

You are currently viewing የከተማዋ የዕድገት መሰላል

የሁለንተናዊ ብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ከተማን እየገነባን ነው

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

.የመዲናዋ ገቢ በ2010 በጀት ዓመት ከነበረበት 33 ቢሊዮን ብር በ2017 በጀት ዓመት ወደ 233 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱም ተጠቁሟል

.ግብርን ሳይሸሽጉ መክፈል ጥቅሙ ለራስ መሆኑን ምስጉን ግብር ከፋዮች ተናግረዋል

ግብር የዘመናዊ ከተሞች የደም ሥር ነው፤ ለሀገራት ሁለንተናዊ የከፍታና ዝቅታ መለኪያ በመሆን ስለማገልገሉ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በሰው ልጆች የስልጣኔ ታሪክም የእህል እና የጉልበት መዋጮ ሲያስገብሩ ከነበሩ ጥንታዊ ከተሞች እስከ ዛሬው የዲጂታል ዘመን ድረስ የዘለቀ ገድል አለው ግብር፡፡

በከተሞች መንገዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የውሃ አቅርቦትን፣ የጤና ማዕከላትን፣ የፀጥታና ደህንነት አስጠባቂዎችን፣ ልዩ ልዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እና መሰል ለሰው ልጆች ሕይወት መጣፈጥ አስፈላጊ የሆኑ የልማት ቅመሞችን ተጠቅሞ የዜጎችን ምቾትና ደህንነት፣ ክብር እና ከፍታን በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለማንበር የግብር ድርሻ ወሳኝ ነው፤ ይላሉ ጀርመናዊው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ኤ. ሙስግሬቭ እ.ኤ.አ በ1959 የመንግስት ፋይናንስ ጽንሰ-ሐሳብ (Theory of Public Finance) በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፋቸው፡፡

በከተሞች ኢኮኖሚ ላይ ያተኮሩ ከአስር በላይ ጥናታዊ የምርምር መፅሐፍትንና በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ የታተሙ የምርምር ፅሑፎችን ያበረከቱት እኚህ ምሁር፣ የመንግስት ፋይናንስ ፅንሰ ሀሳብ አፍላቂዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ግብር የከተሞችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ከፍታ ለማረጋገጥ አስፈላጊ ከሆኑት ወሳኝ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ግብር የከተሞችን ሕይወት ማስቀጠያ እስትንፋስ፣ ለዘመን ዘመናትም ነፍስ ዘርተው እንዲኖሩ ለዕድገታቸው የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማድረሻ የደም ሥር ነውም ይላሉ፡፡

የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ ነሐሴ 1977 (The Incidence of Urban Property Taxation in Developing Countries) በሚል ርዕስ ባሰፈረው መረጃ እንደተመላከተው ግብር፣ ለከተሞች ሕልውና ወሳኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ቀጣዮቹን አምስት ነጥቦች በአስረጅነት አስቀምጧል፡፡ እነዚህም ቋሚ የግብር ገቢ ከሌለ ከተሞች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን የሚያፋጥኑ ዋና ዋና መሠረተ ልማቶችን ማቅረብ አይችሉም፤ ህዝብን የሚጠቅሙ ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ይቸገራሉ፤ በፍትሐዊነት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስርን ማጎልበት ያቅታቸዋል፤ በገንዘብ አቅምና በሌሎች ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ራስን በራስ የማስተዳደር እና ልዩ ልዩ ችግሮችን የመቋቋም አቅምን  ያጣሉ፤ እንዲሁም በግብር ከፋዩ ተሳትፎ በመታገዝ ለሁሉም ምቹ የሆነ አስተዳደራዊ ስርዓትን ለማስፈን ይቸገራሉ፡፡

መረጃው ከሆነ ግብርን በአግባቡ በመሰብሰብ፣ አዋጭና ዘመናዊ አሰራሮችን በመዘርጋት፣ ለግብር ከፋዩ ቀላል አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ፣ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ስለ ግብርና ሀገራዊ ጠቀሜታው ግንዛቤ በመፍጠር እንዲሁም ለምስጉን ግብር ከፋዮች የተለያዩ ድጋፎችን፣ ሽልማቶችን እና ዕውቅናዎችን በመስጠት ሁለንተናዊ ከፍታቸውን ማላቅ ከቻሉ የዓለማችን ከተሞች መካከል ሲንጋፖር፣ ሴኡል እና ቦጎታን በዋቢነት አንስቷል፡፡

በከተሞች ዕድገትና ግብር ዙሪያ የዓለም ታሪክ እና ልምድ እንደሚያሳየው ዜጎች ግብር በታማኝነትና በወቅቱ ሲከፍሉ እና የየአካባቢው መንግስታትም የተሰበሰበውን ግብር በግልፅ እና በብቃት ሲጠቀሙበት ከተሞች በፍጥነት ያድጋሉ የሚሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) ለዚህም በአጭር ዓመታት ውስጥ ማደግ ከቻሉ ከተሞች መካከል ከደቡብ ኮሪያ ሴኡልን፣ ከሲንጋፖር የሲንጋፖር ከተማን እንዲሁም ከሲዊዲን የስቶክሆልም ከተሞችን ፈጣን ዕድገት በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡

አዲስ አበባም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት ላይ መሆኗን የተናገሩት መምህር ይንገስ (ዶ/ር) ይህም ከምታገኘው ከፍ ያለ የግብር ገቢ፤ ይህንን ግብርም ለሚገባው መሰረተ ልማት ማዋል በመቻሉ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ግብርን በታማኝነት መክፈል የበለፀገች ከተማን ለመገንባት መሰረት ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት መምህሩ፣ ሀገር ለስራ የሚተጉና ሰርተው ካገኙት ላይ የሀገርን ድርሻ በታማኝነት ግብር የሚከፍሉ ዜጎች ያስፈልጓታል፡፡ ይህም ዞሮ ዞሮ ለማህበረሰቡ ምቾት የሚሆኑ ልማቶችን ለመገንባት የሚውል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማን በዋቢነት ማንሳት እንችላለን፡፡ ይህም ዕድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት ከሚያደርጋቸው አሰራርን ቀለል የማድረግ፣ ዕውቅናና ሽልማትን ከመስጠት ባሻገር ማህበረሰቡ ግብሩን በታማኝነት የመክፈል ልምዱን ከፍ ማድረግ እንዳለበትም መክረዋል፡፡

ባሳለፍነው ሐሙስም ጥቅምት 6 ቀን 2018 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ “ግብር ለሃገር ክብር” በሚል መሪ ቃል ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች እና ግብር ከፋዮች በተገኙበት የሽልማት እና የእውቅና መርኃ ግብር በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል አካሂዷል፡፡ በዚሁ ዕለት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢ እድገት ከለውጡ ወዲህ እመርታዊ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለአብነትም በ2010 በጀት ዓመት መጨረሻ 33 ቢሊዮን ብር የነበረው የገቢ አሰባሰብ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 233 ቢሊዮን ብር ማደጉን  አስታውሰዋል። የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ87 ቢሊዮን ብር እድገት ማሳየቱንም ጠቅሰዋል። ይህንን እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ የሪፎርም ስራዎች መሰራታቸውን የጠቆሙት አቶ ቢኒያም፣ የገቢ እድገቱ እንዲመዘገብ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

እንደ ከተማ ለታማኝ ግብር ከፋዮች የተደረገውን ዕውቅናና ሽልማት አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክትም ከተማዋ ከታማኝ ግብር ከፋዮች በምትሰበስበው ገቢ በአስደናቂ ሁኔታ የገነባቻቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማት፣ የህዝቡን የኑሮ ጫና ያቀለሉ ስራዎች፣ የተማሪዎች ምገባ እና መሰል ስራዎች ከተማዋን ለቢዝነስ እና ለመኖር የተመቸች ንፁህ፣ ጤናማ አካባቢ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ተመራጭና ተወዳዳሪ እንድትሆን እንዳስቻላትም ገልፀዋል፡፡

በቀጣይ በግብር አሰባሰብ ዙሪያ የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጡን ዲጂታላይዝ በማድረግ፣ በማዘመን እና ተጠያቂነትን በማስፈን ክፍተቶችን እየሞላን፣ ህፀጾችን እያረምን የሁለንተናዊ ብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ከተማን እየገነባን ነው ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ለሽልማትና ለእውቅና የበቃችሁ ግብር ከፋዮቻችን ለታማኝነታችሁ ምስጋናዬ የላቀ ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ በተለይም የወርቅ እና የፕላቲኒየም ደረጃ ግብር ከፋዮች የዘርፉ አምባሳደሮቻችን በመሆናችሁ በከተማችን በየትኛውም መንግስታዊ አገልግሎት እና ኩነት የቅድሚያ ቅድሚያ እንድትስተናገዱ እና “VIP” ፕሮቶኮል እንዲሰጣችሁ መወሰናችንን ስገልፅ ሌሎችም የእናንተን አርአያነት እንደሚከተሉ በማመን ነውም ብለዋል፡፡

መምህር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) እንደሚሉት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ ለምስጉን ግብር ከፋዮች ዕውቅና እና ሽልማት መሰጠቱ የበለጠ ግብራቸውን በአግባቡ እንዲከፍሉ፣ ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ፣ ሌሎች ምስጉን ግብር ከፋዮች እንዲበራከቱ የሚያነቃቃ እና ለሁሉም ምቹ የሆነች ከተማና ሀገርን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የበለጠ የሚያግዝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በእውቅናና ሽልማት መርኃ ግብሩ የተገኙት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ ከተሞች ምሳሌ እንድትሆን የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

ሀገርን ከድህነት ለማላቀቅና ልማትን ለማረጋገጥ የግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ተቀናጅቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሱት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ በከተሞች እድገት፣ በወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ዘርፎች ለተመዘገቡት ጉልህ ስኬቶች የታማኝ ግብር ከፋዮች ሚና ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ እውቅናና ሽልማት ከተሰጣቸው ምስጉን ግብር ከፋዮች መካከል  ደረጀ አስናቀ ወልደሚካኤል የመድኃኒት አስመጭ አንዱ ነው፡፡ የድርጅቱ ኃላፊ አቶ ደረጀ አስናቀ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት ድርጅታቸው ለአምስት ተከታታይ ዓመታት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቶታል፡፡

እንደ ዜጋ ግብርን ሳይደብቁ በወቅቱና በታማኝነት በመክፈላቸው ከከተማ አስተዳደሩ ዕውቅናና ሽልማት ማግኘታቸው ከፍ ያለ ደስታና ለበለጠ ስራ እንዲተጉ መነቃቃትን እንደፈጠረላቸውም አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡ አቶ ደረጀ እንደሚሉት ግብርን ሳይደብቁ በወቅቱ መክፈል ጥቅሙ ለራስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በአዲስ አበባ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ልማቶች የተከናወኑት ከምስጉን ግብር ከፋዮች በሚሰበሰብ ገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ግብርን ሳይደብቁ በወቅቱ መክፈል ለሁላችንም ተጠቃሚነት፣ ለከተማችን እና ለሀገራችን ሁለንተናዊ ከፍታ ያለው ድርሻ ከፍ ያለ በመሆኑ ሁሉም በወቅቱና በታማኝነት ግብር መክፈል ይኖርበታል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review