ለከሳሽ ያልተመቸ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ

You are currently viewing ለከሳሽ ያልተመቸ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ

ኢትዮጵያ የምትከተለው የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የላቀ ውጤት እንዲያስገኝላት ሁሉም ዜጎች በየፊናቸው መተባበር እንዳለባቸው ተጠቁሟል

ኢትዮጵያ የአፍሪካን በርሃማ ስፍራዎች ከዘመን ዘመናት ጥም የሚያረካ ውሃን ብቻ ሳይሆን ነፃነትንም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ያካፈለች ድንቅ ሀገር ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ የዓድዋ ድል ምስክር ነው፡፡ ከቅርብ ዘመን ታሪክም ብንነሳ ከዳርፉር እስከ ኮሪያ የተሻገረ እና በደም የተከፈለ ራስን ብቻ ሳይሆን ጎረቤትንም ሌላውንም፣ ሁሉንም ተጠቃሚ ለሚያደርግ ዕድገትና ሁለንተናዊ ሰላም ቀድሞ የመቆም ገድል አላት፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በፉክክር እና በትብብር መካከል ሚዛን በመጠበቅ፣ ተቃርኖዎችን በማስታረቅ የሚጓዝ መሆን እንዳለበት ታምኖበት በዚሁ ስልት እየተሰራ ይገኛል። በተጨማሪም ሀገራዊ ክብርን ያስቀደመ፣ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ ጎረቤት ሀገራትን ያስቀደመ የውጭ ግንኙነት፣ ቀጣናዊ ትብብርና የኢኮኖሚ ውህደትን ያስቀደሙ ነጥቦች ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራባቸው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አንኳር ጉዳዮች ስለመሆናቸው በፖሊሲ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል፡፡

ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እሳቤ የሚመነጨው ጥቅምን ከማሳደድ ሳይሆን መልካም ትብብርን ከማስቀደም ነው ብላ ታምናለች። በመሆኑም ከሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ባደረገ መልኩ ነው፡፡ በዚህ ስልት አሸናፊ የሆነችባቸው በርካታ ድሎች አሏት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በተቃራኒው ግብፅ እኔ ብቻ ልጠቀም የምትል ሀገር ናት፤ ይህን በተግባርም አሳይታለች፤ እያንዳንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት በተደረገ ቁጥር ክስ ስታቀርብ ቆይታለች፤ ኢትዮጵያን በፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ከስሳ የውይይት አጀንዳ ማሟሻ ስታደርጋት መቆየቷ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ አሁንም ከክስ ወደኋላ አላለችም፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ከትናንት እስከ ዛሬ የዘለቀ ሀብቶችን በጋራ የመጠቀም ቀናኢ አመለካከት አለ፤ ለዚህም ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከፍ ብለንም እንደጠቀስነው ለዘመናት ከነ ሙሉ ክብሩ የሚፈስሰውን የዓባይ ወንዝ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ አልምታ እውን ያደረገችው የህዳሴው ግድብ ምስክር ነው፡፡

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ (ኤን.ቢ.አይ) እ.ኤ.አ በ1999 የተቋቋመ ሲሆን፣ በተፋሰሱ አባል ሀገራት መካከል የናይል ወንዝን በጋራ በማስተዋወቅ እና በማስተዳደር ላይ የተመሰረተ ዓላማ ያለው ነው። በመሰረታዊነት የናይል ውሃ ‘ፍትሐዊ እና ዘላቂነት ያለው አጠቃቀም’ በሚለው መርህ መሰረት የኢኮኖሚ እድገትን፣ ክልላዊ ሰላምን እና የአካባቢ ጥበቃን ለማጎልበት ነው የተመሰረተው። ይህ ደግሞ ዘመናዊና ፍትሐዊ አስተሳሰብን የተከተለ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ፅኑ አቋም ጋር የተወዳጀ ነው፡፡

85 በመቶ የሚሆነው የናይል ውሃ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሐዊ እና ልማት ተኮር የሆነ ​​አጠቃቀምን ትደግፋለች። በመሆኑም የጋራ ኃላፊነት እና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በመደገፍ አንድ ሀገር ብቻ ወንዙን በብቸኝነት ሊቆጣጠር እንደማይገባ ሀገሪቱ አፅንኦት ሰጥታለች ይላል፣ “በዓባይ ተፋሰስ የውሃ መጋራት ተግዳሮቶች፣ ጂኦ ፖለቲካ መቀየር እና የአየር ንብረት ለውጥ።” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ 2011 በሃይድሮሎጂካል ሳይንስ ጆርናል የታተመ ጥናታዊ ፅሑፍ፡፡

በርግጥም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ልማት ላይ ያላት ሚና ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንታዊ መንግሥቶቿ ጀምሮ እስከ አሁን ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች የአፍሪካን የታሪክ ሂደት ባማረ መልኩ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውታለች የሚሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካና የአውሮፓ ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ሽመልስ ኃይሉ፣ የዓለም አቀፍ የሀገራት ግንኙነት የሚመሰረተው በጋራ ትብብር ወይም በጋራ ፍላጎት ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሀገራት ሀብት ስላላቸው ወይም የኢኮኖሚ፣ የኢንዱስትሪና የተለያዩ ነገሮች ስላሏቸው ያላቸውን አቅም ተጠቅመው ሌሎች፣ ላይ ጫና በመፍጠር የማይገባቸውን ጉዳዮች ጭምር ለመውሰድ ወይም ለማግኘት የሚሄዱበት አግባብም እንዳለም የጠቀሱት አቶ ሽመልስ፣ ለዚህም ሲባል ዓለም ፍትሐዊ ናት ተብሎ እንደማይታመን ተናግረዋል፡፡

ዓለም ላይ አንዳንዶች ኢ- ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ግፊት እያደረጉ የሚፈልጉትን ነገር ሲያገኙ ሌሎቹ ደግሞ ፍትሐዊ ዓለም መምጣት አለበት፤ ለዓለም ፍትህ ይገባል፤ የዓለምን ሀብት እኩልና በፍትሐዊ መንገድ በትብብር መጠቀም አለብን ብለው ያስባሉ፤ ያሉት አቶ ሽመልስ፣ የግብፅ እና የኢትዮጵያ ግንኙነትም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ማየት እንደሚቻል ነው ያስረዱት፡፡

መንግስታት ቢቀያየሩም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ጉልህ ልዩነት እንደማይመጣ አውስተው፣ ከእነዚህም አንዱ ዓለም ላይም ሆነ አካባቢያችን ላይ ፍትሐዊ የሆነ ግንኙነት መኖር አለበት የሚለው ነው፡፡ ለአፍሪካ ፍትህ በፀጥታው ምክር ቤትም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋማት እና ህብረቶች ውክልና ያስፈልጋታል፤ የጋራ ሀብቶችን በፍትሐዊና በትብብር መጠቀም ይኖርባታል የሚል ፅኑ አቋም እንዳላትም ጠቅሰዋል፡፡

ግብፅ ደግሞ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል አቋም ነው የምታንፀባርቀው የሚሉት አቶ ሽመልስ፣ ለዚህ ደግሞ የዓባይ ውሃ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ምንም እንኳን 85 በመቶ በላይ የሚሆነው ውሃ ከኢትዮጵያ የሚመነጭ ቢሆንም ያንን በመካድና ዓለምንም በመሸወድ በኢ-ፍትሐዊነት መንገድ ወንዙን ስትጠቀምበት እንደኖረችም አውስተዋል፡፡

የግብፅ ዓላማ ከዚህም በላይ እንደነበር የገለፁት አቶ ሽመልስ፣ የዓባይን ምንጭ ለመቆጣጠር የተለያዩ ጦርነቶችን ኢትዮጵያ ላይ መክፈታቸውን ታሪካዊ ድርሳናት ይመሰክራሉ፤ በተለይም በጉራ እና በጉንደት የከፈቱት ጦርነት በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ቢጠናቀቁም ዓላማቸው ግን ቀላል አልነበረም ብለዋል።

ከጉራ እና ጉንደት ድሎች በኋላ ግብፅ ኢትዮጵያን በቀጥታ መውጋት እንደማይቻላት በመገንዘብ ውስጣዊ የፖለቲካ ክፍፍሎችን በመጠቀም ኢትዮጵያን ደካማና የተከፋፋለች ሀገር ማድረግ፣ እንዲሁም ዓለም ላይ ያላቸውን የፖለቲካ ተፅዕኖ ተጠቅመው የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ ብድርና የተለያዩ ድጋፎችን እንዳይሰጡ በማድረግ ተፅዕኖ ስታሳድር ቆይታለችም ብለዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ሀገራት በአንድ በኩል ለዓለም አቀፍ እውቅና ትብብር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ እያደረጉ በሌላ በኩል ደግሞ ውስጣዊ አቅማቸውን በማጠናከር ተፅዕኖዎችን መቋቋም አለባቸው ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ ተጉዛ ውጤት አግኝታለች፤ ለዚህ ማሳያ ከሆኑት መካከል የህዳሴው ግድብ አንዱ ነው፡፡ ይህ ግድብ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነውን ሀብት የመጠቀም መብቷን የምታሳይበት ብቻ ሳይሆን ዓለም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ማስፈን እንዳለባት የምትመሰክርበት ድል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

አቶ ሽመልስ በማብራሪያቸው፣ ግብፅም እየሄደችበት ያለው ኢ-ፍትሐዊ መንገድ መሆኑን ገልፀው፣ ዓለም ላይ ያላትን ተፅዕኖና ስትራቴጂክ ጥቅሟን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅማ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ላልተገባ ዓላማ እየተጠቀመች ኢትዮጵያ የራሷንና የጋራ የሆነውን ሀብት እንዳትጠቀም ተፅዕኖ የምትፈጥርበት መንገድ የውሸትና ኢ-ፍትሐዊ የሆነ አካሔድ ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን እንደዚህ አይነት የውሸት አካሄዶች ኢትዮጵያ ውስጧን ባረጋጋች ቁጥርና ብሔራዊ አቅሟን ካጠናከረች አይቀጥሉም ባይ ናቸው፡፡ ለዚህም እስከዛሬ ድረስ የናይል ውሃ ከግብፅ እንደሚነሳ፣ ውሃው ህይወታቸው እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ አላግባብ እንደምትጠቀምበት የሚያትት የተሳሳተ ትርክት ለዜጎቿ ስትመግብ ኖራለች፤ ዓለምንም ስታታልል ቆይታለች፤ አሁን ታላቁ የህዳሴ ግድብ መገንባት የዐባይ ወንዝ ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኑ ገሃድ ወጣ፤ ይህም ግብፅን በእጅጉ እንዳበሳጫትም ገልፀዋል፡፡

ለወደፊቱም ቢሆን ኢትዮጵያ ስራዎችን እየሰራች የግብፅን ውሸትና ኢ-ፍትሐዊ እንቅስቃሴዎችን ለዓለም እያሳየች ትሄዳለች ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ለአብነትም በተደጋጋሚ መድረኮች ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የግብፅን ኢ-ፍትሐዊነት ለዓለም እያጋለጠች እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የልማት ጉዞዋን ዓለም በሚገባ ተረድቶ እንዲደግፋት እያደረገች ቀጥላለች፤ ይህም ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሴኔሳ ደምሴ ግብፆች በቅኝ ግዛት ጊዜ የነበረው ስምምነት ላይ መንጠልጠላቸውን አውስተው፣ ይህ ደግሞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የሚያስኬድ አይደለም ብለዋል፡፡

አክለውም፣ በህዳሴው ግድብ ላይ የምታራምደው አቋም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚያዋጣና ትክክል ያልሆነ ነው ብለዋል፡፡ በመሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበና በዚህ ክፍለ ዘመን ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ብቻ ሳይሆን ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ሌሎችን ጎረቤት ሀገሮችን በማይጎዳ መልኩ የመጠቀም መብት ኢትዮጵያ እንዳላት ይዘነጋሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ዓባይ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ኢትዮጵያም ሀብቷን ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ እንደፈለገች የመጠቀም መብት ስላላት በተግባርም እያደረገች ያለችው ይህንኑ ነው፡፡ ይህም የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚታይበት ነው የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትከተለው መርህ ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ መሆኑን የጠቀሱት መምህር ሴኔሳ፣ የህዳሴው ግድብ በየጊዜው በጎርፍ ለሚሰቃዩት ሱዳኖች እፎይታ ፈጥሯል፡፡ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ህግ መርሆችንና የነበሩ ልምዶችን ተከትላ ነገሮችን ከማስኬድ ውጪ ማንንም የመጉዳት ዓላማ ኖሯት አያውቅም። የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀም መብት አላት፤ ከዚህ አኳያ ግብፅ እያደረገች ያለችው ክስ መሰረተ ቢስ በህግም ያልተደገፈና ወቅቱን ያላገናዘበ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ የጀመረችውን ጠንካራ የዲፕሎማሲ መንገድ አጠናክራ መቀጠል አለባት ሲሉ መክረዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው፣ ለቀጣናዊ ልማትና ለጋራ ብልፅግና ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። በታሪክ መንገድ ላይ ወደ ኋላ መለስ ብንልም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ቁልፍ ተዋናይ እንደነበረች እንመለከታለን፡፡ አሁንም አፍሪካ ችግሮቿን በውይይት እየፈታችና ያላትን ሀብት በጋራ ተጠቅማ የድህነትን ቀንበር ሰባብራ ወደ ብልፅግና ማማ ከፍ ትል ዘንድ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ለሆነ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ቀናኢ ሆና በተምሳሌትነት መቀጠሏንም ገልፀዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ እንዲኖራት ኢትዮጵያ ከትናንት እስከ ዛሬ በደም የተከፈለ መስዋዕትነትም ከፍላለች፡፡ ይህም ለሰላምና ለፍትሐዊነት የቆመች መሆኑን የሚመሰክር ሀቅ ነው። በተለይም እንደ አልሸባብ ያሉ ታጣቂ ቡድኖች እየፈጠሩ ካሉት የፀጥታ ችግሮች እና በአካባቢው እየታየ ካለው አለመረጋጋት አንጻር በሰላም ማስከበርም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ትብብር ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሀገራትም ሆነ ለአፍሪካ ጉልህ አበርክቶ እያደረገች ያለች ሀገር እንደሆነችም ጠቁመዋል፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review