በከተማዋ ከ13 ፓርኮች በተጨማሪ 157 ታሪካዊ ቅርሶችና ሌሎች የቱሪዝም መስህቦች መኖራቸው ተመላክቷል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሀቢታት (ዩ.ኤን ሀቢታት) ከሁለት ዓመት በፊት የከተሞች ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ (The Economic Role of Cities) በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው ከተሞች ከጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት አንፃር ያላቸው ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በተቋሙ መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት ከተሞች ከ80 በመቶ በላይ የዓለምን ጥቅል ምርት (Global GDP) ያመነጫሉ። በኢትዮጵያ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርትም ከተሞች 60 በመቶ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳላት መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸው እንዲጨምር ደግሞ የቱሪዝም ሴክተሩ ድርሻ ከፍ እያለ ስለመምጣቱ ይጠቀሳል፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት በመስጠት አዝጋሚ የነበረውን ጉዞ ወደ ጉልህ የእድገት አንቀሳቃሽ ሞተር መለወጥ መቻሉን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ከተለመዱ ውስን ጉባኤዎች በእጥፍ የላቁ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በስኬት በማስተናገድ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት ላይ እንደምትገኝም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ይናገራሉ። ከወራት በፊት የሀገራት መሪዎችን፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ የአየር ንብረት ተመራማሪዎችን፣ ዓለም አቀፍ የሚዲያ አካላትን ጨምሮ ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች የተሳተፉበት የአየር ንብረት ጉባኤን እዚህ ጋር በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደሚገልጹትም መዲናዋ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ 150 ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በከፍተኛ ስኬት ያስተናገደች ሲሆን፣ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህል ጎብኚዎችንም አስተናግዳለች። በዚህም 143 ቢሊዮን ብር ያህል ሀብት ወደ ከተማዋ ኢኮኖሚ ፈሰስ ሆኗል።
ይህ ቁጥር ከአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ዓመታዊ የኮንፈረንስ አዘጋጅነት እጅግ የላቀ ሲሆን፣ በመዲናዋ እንደ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እውን መሆን ለኮንፈረንስ ቱሪዝም መበራከት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። የዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውም ይገለጻል። ለመሆኑ እንደዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማስተናገድ ለመዲናዋ ያለው ትርጉም ምንድነው? የሴክተሩ የእሳካሁን እንቅስቀሴዎች ምን ይመስላሉ? የኮንፈረንስ ቱሪዝሙን ዕድሎች እንዴት መጠቀም ይገባል? የሚሉና መሰል ጉዳዮችን መፈተሽ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአምስት ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በቀን ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ይገኝበታል ይላል፡፡ በተለይም ሴክተሩ በጊዜ ሂደት የወለደውና አዲስ ጽንሰ ሀሳብ የሆነው በምህፃረ ቃል ማይስ (Meeting Incentives & Conference Exhibition) ተብሎ የሚታወቀው ዘርፍ ላይ ሀገራት አተኩረው በመስራት የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን እያሳደጉበት ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ኮንፈረንስ ቱሪዝም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚኖረው ቀጥተኛ ፋይዳ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ የቱሪዝም ባለሙያው አቶ እንቁ ሙሉጌታ እንደሚሉትም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት እጅግ አመርቂ ነው፡፡ የከተማዋን ገጽታ ማሻሻልና መዝናኛ ቦታዎች የሆኑት እንደ ሸገር ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ እና ወዳጅነት አደባባይ ያሉት ቦታዎች ለእንግዶች የመዝናኛና የመሰብሰቢያ ቦታ በመሆን ለጉባኤው ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል። የእነዚህን ቦታዎች ውበትና አገልግሎት ማሳደግ ተጨማሪ ወጪ እንዲያወጡ ያበረታታል ሲሉም ይገልጻሉ።
አዲስ አበባ የኮንፈረንስ ቱሪዝም የስበት ማዕከል እየሆነች ስለመምጣቷ የምጣኔ ሀብት መምህር ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችንና ዝግጅቶችን የሚያስተናግድ ሀገር፣ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ መድረክ ተሰሚነቱ ይጨምራል ይላሉ። አያይዘውም የኢንዱስትሪ፣ የቴክኖሎጂ፣ የምርትና የአገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ሲዘጋጅ፣ የዕውቀት ሽግግርን ያቀላጥፋል። የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ አማራጮችን ይከፍታል። የንግድና የገበያ ግንኙነቶችን ለመፍጠር፣ ውል ለመፈራረም፣ ሽያጭና ግዢ ለመጀመር መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራል ብለዋል።
የኮንፈረንስ ቱሪዝም በተጨባጭ ይዞት የመጣውን ዕደል ጨምረው ሲያብራሩም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የእደ ጥበብ ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይናገራሉ።
አዲስ አበባ ከዚህ በፊትም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በተደጋጋሚ አስተናግዳለች። ከእነዚህ ልምዶች መረዳት እንደሚቻለው፣ በጉባኤ ወቅት የሚስተናገዱ እንግዶች ለሆቴሎች የገንዘብ ፍሰት ከመፍጠራቸው በተጨማሪ፣ ዘላቂ የንግድ ግንኙነቶች እንዲመሰረቱ ያግዛሉ። በርካታ ሆቴሎች በጉባኤው ላይ ከሚሳተፉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለወደፊትም እንግዶችን የማግኘት ዕድላቸውን ያሰፋሉ።
ዓለም አቀፋዊ ከሆኑ ስብሰባዎች ጋር ተጣምሮ የሚካሄደው በዚህ የቱሪዝም ዘርፍ በአፍሪካ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬኒያ፣ ሩዋንዳ ያሉ ሀገራት ቀዳሚ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በወጣው መረጃ በሩዋንዳ የስብሰባ፣ ኮንፈረንሶች እና ዝግጅቶች ዘርፍ (MICE) አስደናቂ እድገት ያስመዘገበ ሲሆን፣ ከ150 በላይ ጉባኤዎችን ባስተናገደችበት በዚሁ ዓመት ብቻ ከ91 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች ይላል ከሀገሪቱ ቱሪዝም መስሪያ ቤት የተገኘው መረጃ።
ዘርፉ በደንብ ሊሰራባቸው ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳባቸውን ያጋሩት ባለሙያዎቹ እንደሚሉት በተለይም ደረጃቸውን የጠበቁ የኮንፈረንስ ማዕከላትን ቁጥር መጨመር፣ የግል ባለሃብቱ በዘርፉ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግን እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሠው ኃይል እጥረት መቅረፍ ይገባል፡፡ ጨምረውም ጎብኚዎች አስፈላጊ መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉበትን ዘመናዊ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ በቴክኖሎጂ የላቁ እና ለትላልቅ ስብሰባዎች በቂ አቅም ያላቸው አዳራሾችና የሆቴል አገልግሎቶች ሊኖራት ይገባል። ይህ ከተማዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮንፈረንስ ማዕከል ያደርጋታል። ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር የተሻለ ግንኙነት ያለው ዘመናዊ የትራንስፖርት ሥርዓት መዘርጋት (ታክሲ፣ አውቶቡስ፣ የባቡር መስመር) ያስፈልጋል። እንግዶች በከተማዋ ውስጥ በቀላሉና በፍጥነት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የግድ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ቱሪዝምን ለማሳደግ፣ የለሙ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ፣ በዚህም “የእግረ-መንገድ ቱሪዝም” (Stopover Tourism) ተጠቃሚነትን ማሳደግ፣ የከተማዋን አዲስ መለያ የሆነውን “new face of Africa”ን ማስተዋወቅን ያካተተ ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
የተለያዩ የገቢ ማሳደጊያ ስትራቴጂዎችን ተጠቅሞ ለኮንፈረንስ ወደ መዲናዋ የሚመጣውን እንግዳ ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የሚመክሩት አቶ እንቁ ሙሉጌታም፣ ጉባኤው ለሚካሄድባቸው ጥቂት ቀናት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊት እና በኋላም ገቢን ለማስገኘት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አክለውም፣ የቱሪዝም እና የጉብኝት ፓኬጆችን በማዘጋጀት የጉባኤው ተሳታፊዎች ሌሎች የሀገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲጎበኙ ማበረታቻና ማራኪ ጥቅሎችን ማዘጋጀት ይገባል ይላሉ።
በእርግጥም የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ አዲስ አበባ የተለያዩ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የሚገኙባት ከተማ ናት፡፡ በከተማዋ ካሉ 13 ፓርኮች በተጨማሪ ታሪካዊ ሐውልቶች፣ ሙዚየሞች፣ አደባባዮች፣ ድልድዮች፣ ጥንታዊ ቤቶች፣ አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶችን ጨምሮ 157 ታሪካዊ ቅርሶች በቱሪዝም መስህብነት ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ኃይማኖታዊ በዓሎች፣ ጋለሪዎች፣ የገበያ ቦታዎች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶችና የባህል ምሽት ቤቶችም ይገኙበታል፡፡
በጉባኤ ማዕከላት አቅራቢያ የእደ ጥበብ፣ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ የቡና እና የባህል ልብሶች መሸጫ ሱቆች እና ኤግዚቢሽኖች ማደራጀት፣ እንግዶች ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው ስጦታ እንዲገዙ ማበረታታት፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከትላልቅ ሆቴሎች እና የኮንፈረንስ አዘጋጆች ጋር የንግድ ግንኙነት እንዲፈጥሩ የሚያስችል መድረኮችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግም የዘርፉ ምሁራን መክረዋል፡፡
እንግዶች በዲጂታል መንገድ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስችሉ ሥርዓቶች መዘርጋት (ዓለም አቀፍ የክሬዲት ካርዶችን መቀበል፣ የሞባይል ክፍያ ሥርዓት) በአንድ ቦታ ሁሉንም የቱሪዝም መረጃ እና አገልግሎት (ኢ-ቪዛ፣ የጉብኝት ቦታዎች፣ የሆቴል መያዣ) የሚያገኙበት የሞባይል መተግበሪያ ማዘጋጀት እንደሚገባም አክለው ባለሙያዎቹ መክረዋል።
የ‘The growth of Meetings, incentive, conferences and exhibition industry in Africa’ ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጁ ክዋኪ ዶንኮርም እንደሚገልፁት ኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚሰጠው ጥቅም የቱሪዝም ገቢ ብቻ አይደለም። የጉባኤውን መድረክ በመጠቀም የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለውጭ ባለሀብቶች ለማስተዋወቅ ያስችላል። እንደ ግብርና፣ ማምረቻ፣ ማዕድን እና አይ.ሲ.ቲ ባሉ ዘርፎች የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን ለውጪ ባለሀብቶች ለማስተዋወቅም የሚፈጥረው ዕድል ከፍተኛ ስለመሆኑ ያብራራሉ።
ከዚህ አንጻር ጉባኤዎቹ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን እና ምሁራንን ወደ አዲስ አበባ ስለሚያመጡ፣ የሀገር ውስጥ ምሁራንና የንግዱ ማህበረሰብ ከአዳዲስ እውቀቶች፣ ቴክኖሎጂዎች እና የተሻሉ አሠራሮች እንዲማሩ ዕድል ይፈጥራል። በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰሩ ሰዎች የዓለም አቀፍ አገልግሎት ደረጃዎችን እንዲያሟሉ ስልጠናና ድጋፍ መስጠት ሌላኛው የዘርፉ በረከት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት እ.ኤ.አ በ2024 የዓለም አቀፍ የማይስ ኢንዱስትሪ ገቢ ከ1 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደነበር ይገመታል። ይህ ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሆን፣ እስከ 2032 ድረስም ወደ 2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል፡፡ እንደ ባንኮክ፣ ዱባይ፣ ኒውዮርክ እና ከአፍሪካም እንደ ጆሃንስበርግ እና ናይሮቢ ያሉ ከተሞች ከኮንፈረንስ ቱሪዝም እና ተያያዥ ከሆኑት የአገልግሎት ዘርፎች ተጠቃሚ ከተሞች ናቸው፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ