የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት በከተማዋ የመግቢያ በሮች የግብርና ምርቶች ማከፋፈያ የገበያ ማዕከላትን ገንብቶ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጉን የዝግጅት ክፍላችን ቅኝት ባደረገባቸው ማዕከላት ያነጋገርናቸው ነጋዴዎችና ሸማቾች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡
ወይዘሮ ወርቄ ሙሉአለም የለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች ገበያ ማዕከል አትክልትና ፍራፍሬ ሲሸምቱ ነው ያገኘናቸው፡፡ በማዕከሉ የሸመቱት ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ካሮት እንዲሁም ጎመን የአቅርቦት ችግር እንደሌለው እና ዋጋውም ውጭ ከሚሸጠው ጋር ሲነፃፀር የ10 እና 15 ብር ቅናሽ እንዳለው ነግረውናል፡፡
መንግስት የገበያ ማዕከላትን በየአካባቢው መገንባቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቶልናል፡፡ ከመኖሪያ አካባቢያችን ሳንርቅ በቅርበት በፈለግነው ሰዓት ትኩስ ምርት መሸመት አስችሎናል፤ እንደዚህ አይነት ማዕከል በየአካባቢው በብዛት ቢገነቡ ህብረተሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል አጋዥ ናቸው ሲሉም ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
ሌላኛዋ፤ የግብርና ምርቶች የሆኑትን ጤፍ፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ደግሞ ዘይትም ሆነ ዱቄት ከማዕከሉ እንደሚሸምቱ የነገሩን ወይዘሮ ሃያት አብደላ ናቸው፡፡ ወይዘሮዋ እንደሚሉት ማዕከሉ ስራ ከጀመረ ጀምሮ ጤፍ የሚገዙት ከማዕከሉ መሆኑን ነው፡፡
“አንደኛ ደረጃ ጤፍ በኪሎ ከ120 ብር እስከ 125 ብር እንገዛለን፡፡ ከማዕከሉ ውጭ ግን የ125 ብሩ ጤፍ እስከ 140 ብር ነው የሚሸጠው፡፡ በማዕከሉ የምፈልገውን ጤፍ መርጬ ገዝቼ እሄዳለሁ እጥረት ኖሮ ሳልገዛ የተመለስኩበት ጊዜ የለም፡፡ ዋጋውም ቢሆን ከውጭው ጋር በአንድ ኪሎ ላይ ከ10 እስከ 15 ብር ልዩነት አለው፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ልዩነት ነው። ሌሎች እንደ እኔ አይነት ሸማቾች በቅናሽ በማዕከሉ እንዲሸምቱ እላለሁ” ሲሉ ማዕከሉ ከሚያመጣቸው ምርቶች ተጠቃሚ ቢሆኑ ይላሉ፡፡

በማዕከሉ በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ተሰማርተው ያገኘናቸው ወይዘሮ ፍሬህይወት ሽመልስ ናቸው፡፡ “ወደ ማዕከሉ ከተቀላቀልን ጀምሮ በበዓላት ወቅት በተለየ ሁኔታ የፍጆታ እቃዎች እንደ ዘይት፣ ዱቄት፣ ስኳር፣ ቡና፣ በርበሬ እንዲሁም ጤፍና ጥራጥሬዎች የማህበረሰቡም ፍላጎት በዚያው ልክ ስለሚጨምር በብዛት እናስገባለን፡፡ ጤፉ የራሳችን ምርት ነው፤ ሌሎች ሸማቾች መጥተው አጥተው የሚመለሱት ምንም ነገር የለም፡፡ ዋጋውም ቢሆን ለበዓላት ወቅት የይርጋ ጨፌ ቡና 950 ብር፣ በቅርብ ጊዜ ወደ ማዕከሉም ስለመጣን በራሳችን ትራንስፖርት እና ምርት ስለሆነ የተጋነነ የዋጋ ጭማሬ አልታየም። በበዓላት ሰሞን በሚሸጥበት ዋጋ ነው አሁን እየተሸጠ ያለው፡፡ ይህ ደግሞ የማህበረሰቡን ፍላጎት ያማከለ እና ውጭ ላይ ከሚሸጠው ዋጋ ቅናሽ ነው” ይላሉ፡፡
አንዳንድ ከሚመጡበት ቦታ ከሚጨምሩ እንደ ስኳርና ቡና በስተቀር ዘይት መቀነስ እንጂ ጭማሬ አላሳየም፤ ጤፍ ደግሞ በበዓሉ ተመሳሳይ ዋጋ በኪሎ ከ110 ብር እስከ 125 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ማህበረሰቡም ደስተኛ ሆኖ ነው የሚሸምተው፡፡
ከራሳችን ጥቅም ይልቅ የህዝቡን ጥቅም ነው የምናስቀድመው የሚሉት ነጋዴዋ፤ በዚህ አጋጣሚም ማህበረሰቡ ከማዕከሉ ውጭ ያለውን ገበያ ጠይቆ ወደ ማዕከሉ መጥቶ ግብይት እንዲፈፅም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሌላኛው በማዕከሉ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ መርከብ ገብረ እግዚአብሔር ናቸው። ሽንኩርት፣ ድንች፣ ጎመን፣ ቲማቲም እና የመሳሰሉ አትክልቶችን እንዲሁም ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ብርቱካንና የመሳሰሉትን ፍራፍሬዎች እንደሚሸጡ ገልፀው ዋጋቸውንም በተመጣጣኝ ሁኔታ እንደሚያቀርቡ አንስተዋል፡፡ ይህንንም በምሳሌነት ውጭ ላይ አቮካዶ እስከ 40 ብር፣ ኤልፎራ ቃሪያ እስከ 120 ብር እየሸጥን ነው ብለዋል፡፡
ምርቶች እንደ አገባባቸው ሊቀንሱና ሊጨምሩ እንደሚችሉ የነገሩን አቶ መርከብ፤ ለበዓላት ሰሞን ገብተው የነበሩ ምርቶች በተሸጡበት ዋጋ በአሁኑ ወቅት እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ምርት ከማሳ እንዲሁም የእነሱ ምርት ካልደረሰ ከተመረቱበት ቦታ ስለሚያመጡ ትኩስ እና ዋጋውም ተመጣጣኝ መሆኑን ነው የነገሩን፡፡
የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ምህረቱ ቀና በበኩላቸው፤ ላለፉት እንቁጣጣሽና መስቀል በዓላት ቀጥታ ከማሳ የተለያዩ ምርቶችን በሰፊው እንዲገቡ በማድረግ ሸማቹ ማህበረሰብ ትኩስ ምርቶችንና ውጭ ላይ ከሚሸጠው ዋጋ ቅናሽ በሆነ መንገድ እንዲሸምት የማድረግ ስራዎች መሰራታቸውን ነግረውናል፡፡
ማዕከሉም የተቋቋመበት ዋና አላማ፤ ውጭ ላይ ካለው ገበያ በቀነሰ ዋጋ በመሸጥ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግና ገበያውን ማረጋጋት ነው። ቅናሹም ከ15 እስከ 20 በመቶ ነው፡፡ በማዕከሉ ለበዓላት ሰሞን የነበረው ዋጋ እና አቅርቦት ልዩነት የለውም ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ምርቶች በበዓላት ሲሸጡበት በነበረው ዋጋ እና አዳዲስ ምርት ሲገባ ደግሞ እየቀነሰ እንደሚሸጥ አንስተዋል፡፡
በበዓላት ወቅት የነበረው አቅርቦትና የዋጋ ተመጣጣኝነት ቀጣይነት እንዲኖረው ከአቅራቢዎች ጋር በመነጋገር ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን የነገሩን አቶ ምህረቱ፤ በየቀኑ የፍጆታ እቃዎቹ በተለጠፈላቸው ዋጋ መሸጣቸውን እንዲሁም ጥራታቸውን ለማረጋገጥ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡
ማህበረሰቡም ከውጭ ያለውን ዋጋ በማነፃፀር ከሩቅ ቦታዎች ሳይቀር በመምጣት ሁሉንም የፍጆታ ምርቶች ሸምቶ በመሄዱ ረገድ በፊት ከነበረው አንፃር ተጠቃሚው እየጨመረ መጥቷል። ብዙ ሰዎችም የሚስተናገዱበት ሆኗል ሲሉ በበዓላት ወቅት የነበረው ዝግጅት የሁልጊዜ መሆኑን ነግረውናል፡፡
ሌላኛው የዝግጅት ክፍላችን ቅኝት ያደረገበት የገበያ ማዕከል የአቃቂ ቃሊቲ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል ነው። በማዕከሉ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ካሮትና ቃሪያ የመሳሰሉትን አትክልቶች ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ አስቴር ካሳ፤ “ማዕከሉ ከተቋቋመ ጀምሮ ግብይት እፈፅማለሁ ለበዓላት ሰሞን የነበረው ዋጋም ሆነ አቅርቦት እስከ አሁን እንደቀጠለ ነው፡፡ እንዲያውም ሽንኩርትና ቃሪያ ከበዓላት በኋላ ቅናሽ ነው፡፡ በተለየ ሁኔታ ቃሪያ በግማሽ ቀንሷል፡፡ በበዓላት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ቀን ቢሆን ተወደደ ከተባለ እንኳን ውጭ ሱቆች ላይ ከምንገዛው ከ20 ብር ያላነሰ በእያንዳንዱ እቃ ላይ ቅናሽ ኖሮት እንሸምታለን፡፡ በዚህም ከማዕከሉ ውጭ ሌላ ጋር ሸምቼ አላውቅም” ሲሉ ነው የነገሩን፡፡
የወይዘሮ አስቴርን ሃሳብ የሚጋሩትና በማዕከሉ ሸቀጣ ሸቀጥ እንደ ምስር፣ አጃ፣ ዘይት እና ስኳር ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ ፀሐይ ሰይድም በማዕከሉ ብዙ ጊዜ እንደሚሸምቱ ነው የገለፁልን፡፡ ጤፍም እንደ ደረጃው ከ110 ብር ጀምሮ እስከ 125 ብር እንደሚሸምቱ ገልፀው፤ “አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሁሉንም የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እየመጣሁ እገዛለሁ፡፡ ለአዲስ ዓመት እና ለመስቀል የነበሩ ግብዓቶች አሁንም አሉ፤ ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡ ዋጋቸውም ከቲማቲም እና ስኳር ውጭ የጨመረ እቃ የለም” ሲሉ ውጭ ከሚሸጠው ጋር የዋጋም ሆነ የጥራት ልዩነት መኖሩን ነው ያጫወቱን፡፡
አቶ ጌቱ ሰይፉ በአቃቂ ቃሊቲ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል ከማሳቸው በማምረት በማዕከሉ ከሚሸጡ ነጋዴዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በማዕከሉ በቂ የምርት አቅርቦት መኖሩን ጠቁመው፤ የተለያዩ የግብርና ምርቶች ለአብነት ከፍራፍሬ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሃባብ፣ ሙዝ፤ ከአትክልት ድንች፣ ቃሪያ፣ ቲማቲም፣ ካሮት፣ ዝንጅብል፣ ሽንኩርትና ሌሎችንም ምርቶች ለሸማቾች ውጭ ላይ ከሚሸጠው በቅናሽ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“በበዓላት ወቅትም በተለይ ለአዲስ ዓመት አቅርቦትም ሆነ የዋጋ ተመጣጣኝነት ነበረ፡፡ እነዚህ ለበዓላት የቀረቡ ምርቶች እንዲሁም ዋጋቸው ከበዓላቱም በኋላ እንደቀጠለ ነው። የሽንኩርት፣ ቃሪያ እና ድንች ዋጋ በወቅቱ ይሸጡበት ከነበረው ዋጋ ቅናሽ አሳይተዋል፡፡ ምርቶቹን ከጉራጌ ዞን ከማሳችን ስለምናመጣቸውም የአቅርቦት ችግር አልገጠመንም፡፡ ዋጋችንም ቢሆን ውጭ ላይ ከሚሸጠው መንግስት ባወጣልን ተመን መሰረት ነው የምንሸጠው፤ አንዳንድ ጊዜ እንዳይበላሽ ከፈራንም ከተመኑ በታች ቀንሰን እንሸጣለን” ሲሉ በማዕከሉ የምርት አቅርቦትም ሆነ የዋጋ ጭማሬ እንደሌለ ገልፀው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልዕክታቸው ነው፡፡
በማዕከሉ በጥራጥሬና ሸቀጣሸቀጥ ንግድ ላይ የተሰማሩት ደግሞ ወይዘሮ ረሂማ ሙክታር ናቸው፡፡ እንደ ምስር፣ አተር፣ አጃ፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች ዘይት፣ ዱቄት፣ ስኳር እና ሌሎችንም ግብዓቶች ለህብረተሰቡ እንደሚያቀርቡ ነግረውናል፡፡ እነዚህ የፍጆታ ምርቶች ከስኳር በስተቀር ለበዓላት ሰሞንም በተሸጡበት ዋጋ እየተሸጡ ይገኛሉ፡፡
ዋጋቸውም ውጭ ላይ ከሚሸጠው እዚህ የምንሸጠው ቅናሽ ነው፡፡ ለዚህም ማህበረሰቡ በጥራትም በዋጋም እንዲሁም በአቅርቦትም ሁሉም በተሟላበት ማዕከላችን መጥተው እንዲሸምቱ አሳስባለሁ ብለዋል፡፡
በማዕከሉ በእንስሳት ተዋፅኦ (አይብ፣ አሳ፣ ዶሮ፣ እንቁላል) ንግድ ላይ የተሰማራችው ወጣት ሃና ተሻለም በበዓላት ወቅት የነበረው ግብይት አሁንም እንደቀጠለ እና በአቅርቦትም ይሁን በዋጋ ላይ ችግር እንደሌለ ገልፃ፤ በተለየ ሁኔታ እንቁላል ውጭ ላይ ከ22 እስከ 25 ብር ሲሸጥ እኛ ጋ በ18 ብር እየሸጥን እንገኛለን ስትል ቅናሽ እንዳለው ተናግራለች፡፡
በማዕከሉ እየተካሄደ ያለውን የስራ እንቅስቃሴና በበዓላት ወቅት የነበረው ለፍጆታ ምርቶች የተሰጠው ትኩረት በሁሉም ጊዜያት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ማብራሪያ የሰጡን የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብሩክታይት መብራቱ ናቸው፡፡ የገበያ ማዕከሉ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል፤ የዋጋ ንረቱን ማረጋጋትን ዓላማ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በማዕከሉ ከሰብል ምርት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ሩዝ፣ ከጥራጥሬ ምስር፣ አተር፤ ከአትክልት ጎመን፣ ድንች፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ቲማቲም፤ ከፍራፍሬ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ እንዲሁም የኢንዱስትሪና የእንስሳት ተዋፅኦዎችን በየአይነቱ በማዕከሉ እንደሚቀርቡና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል።አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሰብል ምርቶችን በአከፋፋይ አርሶ አደሮች ከማሳ በቀጥታ በበቂ ሁኔታ ወደ ማዕከሉ መምጣት መቻሉ ትኩስ እንዲሆን ከማድረጉም በተጨማሪ የደላላ ሰንሰለት ስለሌለው ውጭ ላይ ከሚሸጠው ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ አለው፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በሚልከው የዋጋ ተመን መሰረት ይለጠፋል፤ ግብይቱም በተመኑ መፈፀሙንና አለመፈፀሙን በምን ያህል ዋጋ እንደሆነ በማየት እንዲሁም ሸማቹ ገዝቶ ሲወጣ በስንት ገዛህ ብሎ በመጠየቅ የክትትልና ቁጥጥር ስራ ይሰራል፡፡

ማዕከሉ ያለበት አካባቢ ከዋናው አስፓልት ገባ ያለ በመሆኑ ሁሉም ማህበረሰብ እንዲያውቀውና ተጠቃሚ እንዲሆን ግቢው ውስጥ ኤግዚቢሽን በማድረግ እና ከክፍለ ከተማው ጋር በመሆን የማስተዋወቅ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ነግረውናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍስሀ ጥበቡ በበኩላቸው፤ በከተማዋ መግቢያ በሮች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የግብርና ምርቶች ማከፋፈያ የገበያ ማዕከላት የኑሮ ውድነቱን ጫና በመቀነስ፣ ገበያን በማረጋጋትና በመቆጣጠር ሚናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡
ማዕከላቱ ማህበረሰቡ በዕለት ተዕለት የሚጠቀማቸውን የፍጆታ ምርቶች የደላላን ሰንሰለት በማስቀረት ሸማችና አምራቹን በቀጥታ በማገናኘት ትኩስ እንዲሁም በጥራትና በተመጣጠነ ዋጋ ምርቶቹን ሸማቹ ጋር እንዲደርሱ የሚያደርግ ነው፡፡
በማዕከላቱ የሚፈፀሙ ግብይቶች በመደበኛው ከሚቀርበው የፍጆታ ምርት ዋጋ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ነው ለማህበረሰቡ እየቀረበ ያለው፡፡ በበዓላት ወቅት የፍጆታ ምርቶች ፍላጎት ስለሚጨምር ግብረ ሃይል በማደራጀት አቅርቦቱም እንዲጨምር ይደረጋል እንጂ ዓመቱን ሙሉ የሚካሄደው የግብይት ስርዓት ተመሳሳይ ነው፡፡ በበዓላት ወቅት የሚደረገው አቅርቦት ቀጣይነት እንዲኖረው እና ዋጋውም በወጣለት ተመን መሰረት ግብይት እንዲካሄድ ዓመታዊ እቅድ ታቅዶ በየጊዜው የገበያ ጥናት በማድረግ ነው የሚሰራው፡፡
አጠቃላይ የግብይት ሂደቱ ጤናማ እንዲሆን እና ሸማችና አምራቹ በተረጋጋ መንገድ ግብይት እንዲፈፅም አላስፈላጊ የሆኑ የዋጋ ንረቶች እንዳይከሰቱ፣ እጥረት በሚያጋጥምበትም ወቅት ምርቶች ከየትኛው አካባቢ ሊኖሩ እንደሚችሉ ቦታው ድረስ በመሄድ ጭምር የገበያ ጥናት በማድረግ መረጃ በማደራጀት እጥረት ካለ በልዩ ሁኔታ ወደ ከተማዋ እንዲገቡ የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡
ዓመቱን ሙሉ የአቅርቦት ስራ ሲሰራ ክትትልና ቁጥጥርም አብሮ እንደሚደረግ የነገሩን አቶ ፍስሃ፤ አምራቾች በሚገቡት ውል መሰረት ከስርዓት፣ ከዋጋ እንዲሁም በቂ ምርት ይዘው መግባታቸውን መከታተል ስራ ይሰራል፡፡ በዚህ መሰረትም ይህንን ተግባራዊ ባላደረጉት ላይ በ2017 ዓ.ም 108 በሚሆኑ አምራቾች ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ ከገበያ ትስስር እስከማስወጣት እርምጃ ተወስዷል ብለው፤ ወደፊትም የክትትልና ቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነግረውናል፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ