የመዲናዋ ጥበባዊ መረጃዎች 

You are currently viewing የመዲናዋ ጥበባዊ መረጃዎች 

የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ባለፉት ቀናት በመዲናዋ አዲስ አበባ ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡ ከተሰናዱ ዋና ዋና ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የሙዚቃ ዝግጅት፣ የመጽሐፍት ውይይት፣ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡ 

መጽሐፍት

ዛሬ ‘ቀይ አንበሳ’ በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ ቀይ አንበሳ የተባለው መጽሐፍ በዋናነት ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ድረስ በቆየው የጣሊያን ወረራ ላይ ያተኩራል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ ኮረኔል አልኸንድሮ ዴል ባዬ የተባሉ ኩባዊ ሲሆኑ፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ የጦር ሚኒስቴር ምኒስትር ከነበሩት ራስ ሙሉጌታ ይገዙ ጋር አምባላጌ የዘመተ በጎ ፈቃደኛ መኮንን ናቸው። መጽሐፉ የጣሊያን ጦር በኢትዮጵያ አርበኞች ላይ የፈጸመውን ግፍና መከራ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች በጦር ሜዳ ያደረጉትን ተጋድሎ፣ በጊዜው የነበረው የኢትዮጵያውያን አኗኗርና ማህበራዊ መስተጋብርን የሚመለከቱ አስገራሚ መረጃዎችን የያዘ ነው፡፡ 

‘ቀይ አንበሳ’ የጣሊያን ወረራን በሚመለከት የአይን እማኝ በነበሩ የውጭ የጦር መኮንኖች ከተጻፉ መጽሐፍት መካከል ከ’የሃበሻ ጀብዱ’ ቀጥሎ የሚጠቀስ ተወዳጅ መጽሐፍ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ዛጎል የመጽሐፍ ባንክ ባሰናዳው በዚህ የመጽሐፍ ውይይት ላይ፣ መጽሐፉን ከስፔን ቋንቋ ወደ አማርኛ ቋንቋ የተረጎሙት ተርጓሚ ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ (ዶ/ር) በተጋባዥነት ይቀርባሉ፡፡ ውይይቱ ዛሬ ቅዳሜ  ከ8:00 ሰዓት ጀምሮ ይደረጋል፡፡ የውይይቱ አዘጋጅና አቅራቢ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ሲሆን፣ ውይይቱ የሚካሄድበት ቦታ ደግሞ በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS.) አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡ አድራሻው ቀበና፣ የካቶሊክ ኪዳነምሕረት ትምህርት ቤት ፊት ለፊት፣ ባማ ሕንጻ አጠገብ ይገኛል፡፡

‘ሀገረሰባዊ ትውን ጥበባት’ የተሰኘው መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በዶ/ር አስቴር ሙሉ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ በኢትዮጵያ የተለያዩ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ የትውን ጥበባት ውጤቶችን የተዳሰሰበት የምርምር ሥራ ነው ተብሏል፡፡ ደራሲዋ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፎክሎርና ስነጽሑፍ መምህርት እና ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ያዘጋጁት ይሄ መጽሐፍ በሃገረሰባዊ ትውን ጥበባት የምርምር ዘርፍ ውስጥ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑም ከመጽሃፉ ጀርባ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት ዘሪሁን አስፋው (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡ መጽሐፉ በተለያዩ የመጽሐፍት መደብር ውስጥ ይገኛል ተብሏል፡፡

ሙዚቃ

በሞሰብ የሙዚቃ ማዕከል ውስጥ የሙዚቃ ዝግጅት ይደረጋል፡፡ ነገ እሁድ ጠቅምት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ሶሻል አዲስ ከሞሰብ የሙዚቃ ማዕከል ጋር በመተባበር ያሰናዱት የሙዚቃ ዝግጅት ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ ይቀርባል፡፡ እንዲሁም  በመጪው ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2018 ዓ.ም. ልዩ የመሰንቆ ምሽት ከ10 በላይ ተወዳጅ የመሰንቆ ተጫዋች የሚገኙበት ዝግጅት ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ ይቀርባል ተብሏል፡፡ ሙዚቃው የተሰናዳበት አድራሻ ደግሞ ከ24 ወደ ለም ሆቴል በሚወስደው መንገድ ከሲድራ ሆቴል ከፍ ብሎ መሆኑ ታውቋል፡፡

ሥዕል

የአንጋፋው ሰዓሊ ወርቁ ማሞ ልጅ በሆነችው በወጣቷ ሰዓሊ ገብርኤሏ ወርቁ ማሞ የተዘጋጁ የሥዕል ሥራዎች የሚቀርቡበት “ከልብስ ባሻገር” የሥዕል አውደ ርዕይ ከዛሬ ጀምሮ ለዕይታ ክፍት ይሆናል፡፡ ይህ የሥዕል አውደ ርዕይ በአርታዊ የሥዕል ማሳያ ውስጥ ለዕይታ እንደሚበቃ ኢቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ ፊታችን ጥቅምት 29 ቀን 2018 ዓ.ም በእይታ ላይ ይቆያል ተብሏል።

በሌላ መረጃ ደግሞ፤ የአእምሮ ጤና ላይ ያተኮረ የሥዕል አውደ ርዕይ በመታየት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡ የአእምሮ ጤና ላይ ትኩረት ያደረጉ የሥዕል ሥራዎች የቀረቡበት “Art inspired by mental health” በተሰኘ የሥዕል አውደ ርዕይ ላይ ሲሆን፤ ቦታውም ስድስት ኪሎ በሚገኘው በገብረክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ሙዚየም ውስጥ ነው። በስዕል አውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡ የጥበብ ሥራዎች፤ የአዕምሮ ጤና ትልቅ ትኩረት እንደሚሻ የሚያስገነዝቡ ናቸው ተብሏል፡፡ በዚህ አውደ ርዕይ የሠዓሊ ሶሎሜ ጌታቸው እና የሠዓሊ አለማየሁ ደረሰ ሥዕሎች ቀርበዋል፡፡ አውደርዕዩ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

ቴአትር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ፡፡ ʻ12ቱ እንግዶች’ የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:30 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል፡፡ 11፡30 ሰዓት ደግሞ ʻባሎችና ሚስቶች’ የተሰኘው ቴአትር በዚያው በብሔራዊ ቴአትር ይታያል፡፡ እሁድ በ8፡30 ሰዓት ደግሞ ʻንጉሥ አርማህ’ ቴአትር፣ እንዲሁም ʻእምዩ ብረቷ’ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በዚሁ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል፡፡

በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ደግሞ እሁድ በ8:00 ʻየደመና ዳንኪረኞች’ የተሰኘው ቴአትር ይታያል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ ቀናት በብሄራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ʻሶስቱ አይጦች’፣ ረዕቡ በ11፡30 ʻየቅርብ ሩቅ’ ቴአትር፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ʻሸምጋይ’ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ʻየሕይወት ታሪክ’ በብሄራዊ ቴአትር  ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review