ጥቅምት፣ ውበት እና ኪነት

You are currently viewing ጥቅምት፣ ውበት እና ኪነት

ወራት ልክ እንደ ሰዎች ሁሉ ልዩ ባህርያትና መገለጫዎች አሏቸው፡፡ ይሄ ልዩ መገለጫቸው አንድም ከተፈጥሮ ጋር ባላቸው መስተጋብር ክሱት ይሆናል፡፡ አንድም በወራቱ ውስጥ የሚታዩ መልከ-ብዙ ተፈጥሯዊ ኩነቶች በሰዎች ህይወት ላይ በሚፈጥሩት አዎንታዊና አሉታዊ ገጽታ ይመሰረታል፡፡ ለአብነትም ስለ ክረምት ወራት ስናስብ ወደ አዕምሯችን  ከሚመጡ ኩነቶች መካከል አንዱ ዝናብ ነው፡፡ ዝናቡን ተከትለው የሚመጡት ጭጋግ፣ ቅዝቃዜ፣ ደመና፣ ጭቃ፣ ወንዝ ሙላት… የዚህ የክረምት ዋና ዋና መገለጫዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ተፈጥሯዊ ኩነቶች ደግሞ በሰዎች ዘወትራዊ የሕይወት እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ አለ፡፡ እንዲሁም ከበጋ ወራት የተለየ ድባብና አዕምሯዊ ሁኔታም (ሙድ) በሰዎች ስሜት ላይ ይፈጥራሉ፡፡ ሰዎች ከሚፈጠርባቸው ድባብና የስሜት ሁኔታ በመነሳት ስለ ወራት መገለጫ ባህርያት ይሰጣሉ፡፡

ኢትዮጵያውያንም ለመፀው፣ ለበጋ፣ ለፀደይና ለክረምት ወራት የተለያዩ ስሜቶች አሏቸው፡፡ በተለይ የክረምቱን ማለፍ የሚያውጀው የመስከረም ወር መምጣትን በከፍተኛ ጉጉትና ተስፋ ይቀበሉታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመን የሚለወጠው በዚህ ወር ነው፡፡ እንደ መስቀልና ኢሬቻ ያሉ የአደባባይ በዓሎች በደስታ የሚከበሩትም በዚህ ወር ነው፡፡ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት የሚመለሱትና እንደ ፍርድ ቤት ያሉ መንግስታዊ ተቋማት ስራቸውን እንደገና የሚጀምሩትም በዚሁ ወር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አዳዲስ ዕቅዶችን በመወጠን በአዲስ ሃይል የሚነሳሱትም የመስከረም ወር ድባብን መነሻ በማድረግ ነው፡፡

ምድርም ከወርሃ መስከረም ጀምራ ማሸብረቅ ትጀምራለች፡፡  መስኮች አደይ አበባ ይለብሳሉ፡፡ በክረምት ዝናብ የሞሉ ወንዞች መጉደል ይጀምራሉ፡፡ የደፈረሱ ወንዞችም መጥራት ይጀምራሉ፡፡ ሰማይ ለፈትል እንደተዘጋጀ ጋቢ ትነጣለች። ይህች የመስከረም ድባብ ወደ ወርሃ ጥቅምት ስትሸጋገር ተፈጥሮ ይበልጥ ተውባና ተኳኩላ ትታያለች፡፡ ውበቷ ልክ እንደ ሙሽሮች የፊት ገጽ ይፈካል። መስኮች በአረንጓዴ ያጌጣሉ፡፡ አበቦቹ በየቦታው ፍንድቅድቅ ብለው ተስፋን ያዜማሉ፡፡ ይሄ ድባብ ደግሞ በሰዎች ስሜት ላይ ቀጥታ የመጋባት ሃይል አለው፡፡ በሀገራችን በተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎች ውስጥ ጎልተው የሚሰሙ ዜማዎችና ስንኞች የዚህ ስሜት ነጽብራቅ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ እኛም በዚህ አጭር ጽሑፍ በኢትዮጵያ አውድ ወርሃ ጥቅምትን በኪነ ጥበብ ሥራዎችና በህዝባዊ ሥነ-ቃሎች እንዴት እንደተገለጹ በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡

የአበቦች ሙዚቃ በጥቅምት

የባህል፣ የሰላምና የኪነ ጥበብ ተመራማሪው ወሰን ባዩ (ዶ/ር) ከወርሃ ጥቅምት ጋር በተያያዘ ለዝግጅት ክፍላችን ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ጥቅምትን ከውበትና ከተስፋ ጋር አስተሳስረው እንደሚረዱት ያጫወቱን ወሰን ባዩ (ዶ/ር)፣ በመስከረም የጀመረው አበባ ሙሉ በሙሉ የሚፈካበት ቡቃያው ወደ እሸት የሚያድግበት ጊዜ በመሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ ጥቅምት ከተስፋና ከልምላሜ ጋር ተያይዞ ይወሳል፡፡ ወርሃ ጥቅምት በእሸት፣ በአበባ፣ በውበትና በተስፋ እንደሚመሰልም ተመራማሪው አጫውተውናል፡፡ ጥቅምትን መነሻ ተደርገው የተቀነቀኑ ዜማዎች፣ የተገጠሙ የግጥም ስንኞችና ማህበረሰባዊ ሥነ ቃሎች በአብዛኛው ከውበት፣ ከልምላሜና ከተስፋ ጋር እንደሚተሳሰሩም አጫውተውናል፡፡

በሀገራችን ለፍቅር፣ ለሀገር፣ ለቤተሰብና ለናፍቆት በርካታ ሙዚቃዎች ተሰርተዋል። ስለ ወርሃ መስረከም እና አዲስ ዓመትም እጅግ በርካታ ሙዚቃዎች ተቀንቅነዋል፡፡ ስለ ወርሃ ጥቅምት እና አበባ ከተሰሩ ሙዚቃዎች ውስጥ ደግሞ የአንጋፋው ሙዚቀኛ ነዋይ ደበበ “የጥቅምት አበባ” የተሰኘው ዘመን አይሽሬ ዘፈን በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ሙዚቀኛው በዚህ የጥበብ ሥራው ጥቅምትን ህያው አድርጓታል፡፡ ወርሃ ጥቅምትን ከአበባና ከፍቅር ጋር አሰናኝቶ ዘመን ተሻጋሪ ጥዑም ዜማ አስደምጦናል።

“የጥቅምት አበባ፤ የጥቅምት አበባ፤

የጥቅምት አበባ ነሽ አሉ፤

አወድሽው አካሌን በሙሉ።

የጥቅምት አበባ፤ የጥቅምት አበባ፤

የጥቅምት አበባ ለሽታ

ለኔ ግን ጣልሽብኝ ትዝታ…”እያለ ለተናፋቂዋ ፍቅሩ ያዜምላታል፡፡ በዚህ ውብ ሙዚቃ የጥቅምት አበባ  የማትረሳ እና ሁልጊዜም የምትታወስ መሆኗን፣ የፍቅር ትዝታም እንደዛው መሆኑን ያቀነቅናል፡፡

ድምጻዊ ነዋይ ደበበ የናፈቃት ልጃገረድ እንደ ጥቅምት አበባ መላ አካልን ታውዳለች፡፡ መንፈስን ታድሳለች። የናፈቃትን ውቧ አበባን ለመጎብኘት ‘እንደ ቢራቢሮ ክንፍ አውጥቼ ልምጣ ወይ?’ በማለት መናፈቁን ያዜምላታል። በሙዚቃው ከፍቅሩ ጋር ጠጋ ብሎ ለመወያየት ማረፊያ መፈለጉንም ያወጋናል፡፡

…“ማረፊያ አለ ወይ ፍቅርዬ

እንዳዋይሽ ሚስጥር ጠጋ ብዬ

የጥቅምት አበባ ነሽ

አካል ሰው ነይ ናፈኩሽ

ውበት መአዛሽ ለሽታ

ፍኪልኝ ልቤ ያግኝ ደስታ…“በማለትም ጥቅምትና አበባን፣ እንዲሁም ፍቅርን በማዋሃድ በጥቅምት ወር ብቻም ሳይሆን በየትኛውም ወር እና ዘመን ተደማጭና ተወዳጅ ሙዚቃን አበርክቷል፡፡

ድምጻዊው ፍቅርና የጥቅምት አበባን፣ አንዱ ተወዶ አንዱን መጥላት እንደማይቻል፣ ተፈጥሮም በሃሴት፣ ተፈቃሪዋ ልጃገረድም በውበት የተሞላች መሆኗን በዘፈኑ አንጸባርቋል፡፡

ጥቅምትን በሥነ ጽሑፍ

ጥቅምትና አበባ፣ ጥቅምትና ውበት፣ ጥቅምትና ተስፋን ካሰናኙ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መካከል አንዱ የሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን “አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ” የተሰኘው ግጥሙ ይገኝበታል። በዚህ ግጥም ውስጥ የጥቅምትን ወር ውበት፣ ናፍቆትና እሸት እጅግ ድንቅ በሆኑ ቃላትና ስንኞች ገልጾታል፡፡

“…ተግ ሲል ያንቺ ሽውታ

ብዥ ሲል እንደ አድባር ጥሪ፣ እንደተርብ ቅርስ ሽታ

እንደ እሳት ዳር ተረት ግርሻ፣ እንደ እንቆቅልሽ ትውስታ

የጥቅምት እሸት አወደን፣ ነቃ ደሞ ያንቺ ትዝታ…

አውድማው ተንተረከከ

ሰንበሌጥ ተንተረከከ

ነይ አክርማ እንነቃቅል

ከወንዛችን ሾላ ጠለል

ነይ ጢሎሽ እንንጠላጠል

መስኮቻችን ሰብሎቻችን፥ ግጦሾቻችን አባቱ

የእቴቴ ላሞች አጋቱ

በሮቻችንም አጓሩ፣ ኮርማዎቻችንም ነቁ

ጊደሮቻችን ለጥቃት፣ ለይዘታ ለክብደት በቁ

  የሁዳድ ድርቆሽ ሰፈር፣ ጥገቶቻችን ቦረቁ…

እያለ ጥቅምትን ስዕላዊ በሆነ፣ ወቅቱን በሚያስናፍቅና በትዝታ በሚያስረቀርቅ ቅኔ ከይኖታል፡፡

ጥቅምት በግጥም ብቻም ሳይሆን በአባባል እና በአጠቃላይ ፎክለርንም የሚገለጽ ወር ነው፡፡ ከአባባሎች ውስጥ በጣም ታዋቂው “በጥቅምት አንድ አጥንት” የሚለው ነው፡፡ የጥቅምት ወር ከልምላሜ ፀጋው በተጨማሪ በማለዳው ውርጭ፣ በምሽቱ ቅዝቃዜና በለሊቱ ቁርም ጭምር በደንብ ይታወቃል። እንዲሁም ቀን ቀን የሚወጣው ጠንከር ያለ ፀሐይም ሌላኛው የጥቅምት ወር መገለጫ ነው።

በተጨማሪም “የጥቅምት ማር፣ እሸት ይሸታል እጃችሁ

ያ’ገሬ ወጣቶች ተማሩ እባካችሁ፤ የሚለው ሥነ ቃልም የጥቅምት ወርን ከሚያስታውሱ፣ ወሩ የማርና እሸት ወቅት መሆኑን ከሚያመላክቱ  ሥነ ቃሎች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ ልክ ውብና ማራኪ፣ በተፈጥሮ ጸጋዎች እንደተሞላው ወርሃ ጥቅምት ሁሉ፤ ወጣቶችም ልዩ ስሜት ያላቸው፣ ደስ የሚሉ፣ በተስፋ የተሞሉ፣ መማር እና መመራመር እንዳለባቸውም የሚመክር አባባል ነው፡፡

ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር የተባሉ ጸሐፊ በ2007 ዓ.ም ለንባብ ባበቁት፣ “ኅብረ ብዕር (የብዕር ዘመራ)” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት ደግሞ  ወርሃ ጥቅምት አዕዋፋት፣ ፍራፍሬ እና ጥራጥሬ እንደ ልባቸው እየተመገቡ በጋራም በተናጠልም የሚዘምሩበት፣ የቤት እንስሳት በየቃርሚያው የተረሳ እሸት በመብላት የሚሰበሰቡበት ወር መሆኑን ጽፈዋል፡፡

እዚህጋ ማስታወስ የሚያስፈልገው ኢትዮጵያ ሰፊ መልክዐ ምድር፣ የተለያየ የአየር ንብረት ያላት እንደመሆኗ እሸት በተለያየ  ጊዜም ሊኖር ይችላል፡፡ ለአብነትም በሀገራችን ቆላማ አካባቢዎች እሸት የሚደርሰው ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡

  ከእሸት እና አበባ በተጨማሪ ጥቅምት የማር ወርም ነው፡፡ “ማርን መቁረጥ በጥቅምት” የሚለው የሀገራችን ሥነ ቃል ለዚህ ማሳያ ነው ይላሉ፤ ደራሲ ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር በመጽሐፋቸው፡፡ በእርግጥ ማር ከጥቅምት ሌላ በህዳርም ሆነ በሌሎች ወራት ይቆረጣል፡፡ ታዲያ ግን ከህዳር ሆነ ከሌሎች ወራት ማር ይልቅ የጥቅምት ማር መድኃኒትነት እንዳለው ይታመናል፡፡ በገጠራማው የኢትዮጵያ  አንዳንድ አካባቢዎች ማር በተመቸ  ቀን ብቻ  አይቆረጥም፡፡ ከጥቅምት አጋማሽ በኋላ የአበባ ወቅት የሚያበቃበት፣ ቦታውን ለፍሬ የሚያስረክብበት ቀን ነው ተብሎ በሚታመንበት ሰሞን ማር መቁረጥ የተለመደ መሆኑንም ደራሲ ካህሳይ በመጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡

በአጠቃላይ ጥቅምት ኪነ ጥበባዊ፣ ፎክሎራዊ፣ ተፈጥሯዊና ሌሎችንም መልኮች የያዘ ነው፡፡ በዚህም የጥቅምት ወር በተለያዩ  አካባቢዎች በሚኖሩ የሀገራችን ማህበረሰቦች ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጠውም ነው፡፡ በውበቱ፣ በልምላሜውና  ተስፋን በመቸሩ  ምክንያት  ወርሃ  ጥቅምት  በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጁ ወር ሆኗል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review