የአፍሪካ ተሳትፎ በዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ  

You are currently viewing የአፍሪካ ተሳትፎ በዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ  

ብዙ ሀብት የሚዘወርበት የእግር ኳስ ውድድር የሰው ልጅን ቀልብ መግዛት ከቻሉ ስፖርቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ደግሞ ከእነዚህ ተወዳጅ ውድድሮች መካከል ይገኝበታል፡፡ ከ95 ዓመት በፊት የተመሰረተው እና በአራት ዓመት አንዴ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሁለት ጊዜ ካለመከናወኑ በቀር ከምስረታው ጀምሮ ለ22 ጊዜ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በሜክሲኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደውና ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራትን የሚያሳትፈው የ2026ቱ  የፊፋ የዓለም ዋንጫ በቀጣይ ክረምት ይካሄዳል፡፡ በዚህ ማሻሻያ ምክንያት ለአፍሪካ የተሰጠው ውክልናም ወደ ዘጠኝ ሀገራት ከፍ ያለ ሲሆን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንም (ካፍ) 53 ሀገራትን በምድብ ከፋፍሎ ሲያወዳድር ቆይቷል፡፡ እስካሁን ለዓለም ዋንጫው ማለፋቸውን ካረጋገጡት የአፍሪካ ሀገራት መካከል ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ አልጄሪያ፣ ጋና፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ደቡብ አፍሪካና አይቨሪ ኮስት ሲሆኑ ቀሪ ሶስት ሀገራት ደግሞ በቀጣይ ተለይተው የሚታወቁ ይሆናል፡፡

በአትላንቲክ ውቂያኖስ ውስጥ ከሚገኙ ትንንሽ ደሴቶች አንዷ የሆነችው ኬፕ ቨርዴ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ በትልቁ የዓለም ዋንጫ መድረክ መሳተፏን አረጋግጣለች፡፡ 4 ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያላት ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በ96 ዓመት የዓለም ዋንጫ ታሪክ በመድረኩ የተሳተፈች ትንሿ ሀገርም ሆናለች፡፡ 5 ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ትሪንዳድ እና ቶቤጎ በ2006ቱ የጀርመን ዓለም ዋንጫ ተሳታፊ የነበረችበት በክብረ ወሰንነት ተይዞ የነበረ ቢሆንም አሁን በሌላ ትንሽ ሀገር ተተክታለች ይላል የአፍሪካ ኒውስ ዘገባ፡፡

በአፍሪካ ሀገራት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ አራት ላይ የነበረችው ሀገር ካደረገቻቸው 10 ጨዋታዎች ሰባቱን አሸንፋ በሁለቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርታ በ23 ነጥብ ምድቡን በበላይነት በማጠናቀቅ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊነቷን አረጋግጣለች፡፡ ለሀገሪቱ ዜጎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፊፋ ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ “የሀገራችሁ ሰንደቅ አላማ በትልቁ መድረክ ከፍ ብላ የምትታይበት እና ብሔራዊ መዝሙራችሁ በዓለም የሚሰማበት ይሆናል” ብለዋል፡፡

ለስኬቷ ምስጢር የኬፕ ቨርዴ የዘር ሐረግ ያላቸውን እና በአውሮፓ የሚኖሩ ልጆቿን ማሰባሰቧ እንደሆነ የሚነገርላት ሀገሪቷ በእግር ኳሷ ላይ አተኩራ በመስራቷ 15 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከአህጉሩ ትልቁን መድረክ ተሻግራ በዓለም ዋንጫ ተከስታለች፡፡ ኬፕ ቨርዴ በአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችው በ2013 የደቡብ አፍሪካ ዋንጫ ሲሆን፣ ሁለት ጊዜ ደግሞ ለሩብ ፍጻሜ የደረሰችበትን ውጤት ማስመዝገቧም ይታወሳል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የቀድሞው የኬፕ ቨርዴ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ፔድሮ ሌይታኦ ብሪቶ በአምስት ዓመታት ቆይታው በሁሉም መንገድ የተዋጣለት ቡድን ገንብቶ አዲስ ታሪክ ጽፏል፡፡

የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የሆነችው ሴኔጋል በተረጋጋ የአሰልጣኝነት አመራር (በአሊዩ ሲሴ) እና ለዓመታት በአንድ ላይ የተጫወቱ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ስብስብ ነበራት። በተለይም እንደ ሳዲዮ ማኔ ያሉ ኮከብ ተጫዋቾች መኖራቸው ለቡድኑ ጥንካሬ ሰጥቷቸው ወደ ዓለም ዋንጫው ስለማምራታቸው የዘ ኔሽን ጋዜጣ ዘጋበ ያሳያል፡፡

የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን በዎሊድ ሬግራጉይ መሪነት ቡድኑ በፍጥነት አንድነትን ፈጥሮ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን እንደገነባ እየተነገረለት ይገኛል። በርካታ ተጫዋቾች በአውሮፓ ትላልቅ ሊጎች የሚጫወቱ መሆናቸውና በተለይም በግብ ጠባቂው (ያሲን ቡኑ) እና የመከላከል መስመር (አሽራፍ ሃኪሚ) ላይ ጠንካራ መሆናቸው ለታሪካዊ ስኬት አብቅቷቸዋል። የሬግራጉይ ቡድን በጠንካራ መከላከል ላይ የተመሰረተ (Solid Defensive Structure) እና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ስልት (Counter-Attacking Strategy) መጠቀሙን የሚያብራራው የዘ ኔሽን ጋዜጣ ፀሐፊው ዋለ ጋባዴቦ ነው፡፡

ምድብ ዘጠኝ ላይ የነበረችው ጋና ከ10 ጨዋታ 25 ነጥብ በመሰብሰብ ቀዳሚ ሆና አጠናቅቃለች። ለመጀመሪያ ጊዜ በ2006 የዓለም ዋንጫ የተሳተፈችው ጋና የ2026ቱ አምስተኛ ተሳትፎዋ ይሆናል። እንደ ካሜሩንና ጋና ያሉ ብሔራዊ ቡድኖች ደግሞ በአዳጊዎች ላይ አተኩረው በመስራት የዕድሜ ክልል ቡድኖችን ከወጣትነት ጀምሮ በአግባቡ ማሰልጠን፣ ኮከብ ተጫዋቾች ተፈጥረው ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርሱ እንደረዳቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

የቱኒዚያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫዎች ላይ በቋሚነት ከሚሳተፉ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ነች። በዘንድሮው ውድድር ላይ ባሳየችው ጠንካራ የማጣሪያ ጉዞ (በጥቂት ነጥቦች መሪ ሆና) ያለፉት ውድድሮች ላይ ያጣቻቸውን ጥቂት የጨዋታ ጊዜያትን በማረም ከምድብ ማለፍ ችላለች፡፡

እንደ ሞሐመድ ሳላህ፣ ሪያድ ማህሬዝ የመሳሰሉ ከዋክብትን የያዙት የግብጽ እና የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድኖች በዓለም ዋንጫው ብዙ ርቀት ይጓዛሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡

አፍሪካ በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ መሳተፍ የጀመረችው እ.ኤ.አ በ1934ቱ የዓለም ዋንጫ ግብጽን በመወከል ነበር። ከዚያ በኋላ ለረጅም ዓመታት በአህጉሩ እና በፊፋ መካከል የነበረው ውክልና አለመመጣጠን ምክንያት በውድድሩ ላይ የአፍሪካ ሀገራት ተሳትፎ በጣም አነስተኛ ነበር። እስከ 1970 ዓ.ም ድረስ አፍሪካ በዓለም ዋንጫ የምትወከለው በአንድ ብሔራዊ ቡድን ብቻ ነበር። ከ1982ቱ የዓለም ዋንጫ ጀምሮ ግን የውክልና ድርሻዋ ወደ ሁለት ቡድኖች ከፍ ብሎ ይህም እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ ቀጥሏል። በ1998ቱ ውድድር ደግሞ የአፍሪካ ተወካይ ሀገራት ቁጥር ወደ አምስት ከፍ ብሎ እስከ 2022ቱ የኳታሩ ዓለም ዋንጫ ድረስ ስለመቆየታቸው የስካይ ስፖርት መረጃ ያሳያል፡፡

ምንም እንኳን የአፍሪካ ሀገራት በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ መሳተፍ ከጀመሩ ረጅም ጊዜ ቢሆነውም፣ አህጉሪቱን ወክለው የተሳተፉት ቡድኖች ዋንጫውን ማንሳት ባይችሉም፣ የሚጠቀሱ ታሪካዊ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።

የአፍሪካ ሀገራት በዓለም ዋንጫ የተመዘገበው ከፍተኛው ውጤት ሩብ ፍጻሜ (Quarter Finals) መድረስ ነው። ይህን ታሪካዊ ምዕራፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመዘገበችው ካሜሩን በ1990ው የዓለም ዋንጫ ነበር። በሮጀር ሚላ መሪነት የአፍሪካን ክብር ከፍ ያደረገችው ካሜሩን የዓለምን ትኩረት ስባ ነበር።

የስካይ ስፖርት መረጃ እንደሚያሳው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በ2002ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ በታላቅ ብቃት ተጫውታ ለሁለተኛ ጊዜ ሩብ ፍጻሜ የመድረስ ታሪክ ደግማለች። ሴኔጋል ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ስትሳተፍ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ የሆነችውን ፈረንሳይን በማሸነፍ ታሪክ በመስራት ነበር።

የጋና ብሔራዊ ቡድን እንደዚሁ በ2010 ደቡብ አፍሪካ የዓለም ዋንጫ ላይ አህጉሪቱን ወክላ ሩብ ፍጻሜ የደረሰች ሦስተኛ ሀገር ሆናለች። በተለይም ከኡራጓይ ጋር ባደረገችው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ የማይረሳ ድራማዊ ፍልሚያ በማድረግ በአሳዛኝ ሁኔታ በፍጹም ቅጣት ምት ተሸንፋ ከውድድሩ መሰናበቷ ይታወሳል። በኳታር በተካሄደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ላይ ሞሮኮ ባሳየችው ድንቅ ብቃትና አዲስ ታሪክ በመስራት ወደ ግማሽ ፍጻሜ (Semi-Finals) በመድረስ የአፍሪካን እግር ኳስ ታሪክ በወርቃማ ቀለም ጽፋ  የመጀመሪያዋ ግማሽ ፍፃሜ የደረሰች ሀገር ሆናለች። ይሁንና የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ አህጉረ አፍሪካ በእስካሁኑ ሂደት ያስመዘገበችው ውጤት ከሩብ ፍጻሜ የተሻገረ አይደለም፡፡

የዘ ኔሽን ጋዜጣ ገፀ ድር መረጃ እንደሚያሳየው ካሜሩን፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ቱኒዚያ እና አልጄሪያ አህጉሪቱን ወክለው በዓለም ዋንጫው ተደጋጋሚ ተሳትፎ ያደረጉ ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡ በ2022ቱ የኳታር ዓለም ዋንጫ ላይ አፍሪካን ወክለው የተሳተፉት አምስት ሀገራት ሴኔጋል፣ ሞሮኮ፣ ጋና፣ ካሜሩን እና ቱኒዚያ መሆናቸው ይታወሳል።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review