በዘንድሮው የጣና ፎረም የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ በልዩ ሁኔታ የባለሙያዎች ምክክር እንደሚደረግበት ተነገረ፡፡
“አፍሪካ በተለዋዋጩ ሉላዊ ስርዓት” በሚል የዘንድሮው 11ኛው የጣና ፎረም ከቀጣዩ ጥቅምት 14 አስከ 16/2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
በዚህ ፎረም ላይ የተለያዩ የአፍሪካ መሪዎች፣ የሰላም እና ፀጥታ መልዕክተኞች ምሁራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉም ተነግሯል።
ተሳታፊዎቹ ግጭትን ለማስቀረት የሚረዱ የተሻሉ የመፍትሄ ሀሳቦች የሚያጋሩበት እና ልምድ የሚቀያየሩበት መድረክ እንደሚሆንም ነው የተገለፀው።

ሰለ ዘንድሮው ፎረም አጠቃላይ ሁኔታ መግለጫ የሰጡት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዘሪሁን አበበ፤ ከተወሰነ ዓመት መቋረጥ በኋላ ዘንድሮ የሚደረገው የጣና ፎረም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ልዩ የባለሙያዎች ምክክር ይደረግበታል ብለዋል።
ፎረሙ በአዲሰ አበባ አድዋ ድል መታሰቢያና በባህርዳር ከተሞች የሚካሄድ መሆኑም ነው የተነገረው።
ጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ምክክር የሚደረግበት ሲሆን ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለማመላከት ዓላማ ያደረገ ነው።
በሰላምና ሰጥታ ጉዳዮች ምክክር የሚደረግበት ይህ ፎረም፤ ለፖሊሲ ግበዓት የሚሆኑ ሀሳቦች የሚቀርቡበትና የአፍሪካ ሀገራት በሰላም እና ፀጥታ ዙሪያ ተቀራርበው እንዲሰሩ የሚረዳ ነው።
በአሰግድ ኪዳነማርያም