የቡንደስሊጋው ትልቁ ጨዋታ “ደር ክላሲከር” ዛሬ ይደረጋል

You are currently viewing የቡንደስሊጋው ትልቁ ጨዋታ “ደር ክላሲከር” ዛሬ ይደረጋል

AMN-ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም

ጀርመኖች ሊጋቸውን ለማስተዋወቅ ከፊት የሚያመጡት ጨዋታ “ደር ክላሲከር”ን ነው።

ባየርን ሙኒክ ከ ቦሩሲያ ዶርትመንድ የሚያደርጉት ይህ ጨዋታ ሁሌም በጉጉት ይጠበቃል። “ደር ክላሲከር” ብለው በመሰየም ጨዋታውን ለማግዘፍም ይሞክራሉ። የውድድር ዓመቱን ሳይሸነፉ የጀመሩት ባየርን ሙኒክ እና ቦሩሲያ ዶርትመንድ ዛሬ ለ138ኛ ጊዜ ይገናኛሉ።

ባየርን ሙኒክ በቪንሰንት ኮምፓኒ እየተመሩ ድንቅ የውድድር ጅማሮ አድርገዋል። በሁሉም ውድድሮች 10 ጨዋታ አድርገው በድል ተወጥተዋል። ሙኒክ የመጀመሪያ 10 ጨዋታዎቹን ሲያሸንፍ እ ኤ አ ከ1965 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በሊጉ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች 25 ግብ ከመረብ አሳርፈው ሦስት ብቻ ተቆጥሮባቸዋል። በቡንደስሊጋው ታሪክ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ጨዋታ 25 ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያው ክለብም ሆኗል።

የጀርመኑ ሀያል ክለብ ካስቆጠራቸው 25 የሊግ ግቦች የ11 ባለቤት እንግሊዛዊው አጥቂ ሀሪ ኬን ነው። ዶርትመንድ በቀድሞ የባየርንሙኒክ ተጫዋች እና አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫች እየተመራ ጥሩ ጅማሮ አድርጓል።

በሊጉ ምንም ሽንፈት ያልገጠመው ዶርትመንድ ከስድስት የሊግ ጨዋታ አራቱን አሸንፎ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል። ዶርትመንድ በቡንደስሊጋው ሙኒክን 33 ጊዜ መርታት ችሏል። ባየርን ሙኒክ በየትኛውም ክለብ ይህን ያህል ጨዋታ ተረትቶ አያውቅም።

ቦሩሲያ ዶርትመንድ በዛሬው ጨዋታ ሴርሁ ጉዪራሲን መልሶ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ጉዪራሲ በ2025 ከኪሊያን ምባፔ እና ሀሪ ኬን በመቀጠል ሦስተኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው። ጊኒያዊ አጥቂ 32 ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል። የዛሬው ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 1:30 በአልያንዝ አሬና ይከናወናል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review